የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከፍተኛ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው የአፋር፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሊ፣ ደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እና ትግራይ ክልሎች እየተባባሰ የመጣው የሰብአዊ ቀውስ በእጅጉ አሳሳቢ መሆኑን ገለጸ። ኮሚሽኑ በቅርቡ ይፋ ባደረገው የኢትዮጵያ ዓመታዊ ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርቱ (ከሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. እስከ ሰኔ ወር 2015 ዓ.ም.) በገለጸው መሠረት ለተፈናቃዮችና ለተፈናቃይ ተቀባይ ማኅበረሰቦች ሲቀርብ የነበረው ሰብአዊ እርዳታ ባለፉት ወራት መቀነሱ በእነዚህ ክልሎች ያለውን ሰብአዊ ቀውስ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲባባስ አድርጓል።
ኢሰመኮ በትግራይ ክልል እያካሄደው ባለው የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሥራ ማኅበረሰቡ እና ተፈናቃዮች ዋነኞቹ የሰብአዊ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ሥራቸውን በማቋረጣቸው ከአራት እስከ ሰባት ወራት ለቆየ ጊዜ ሰብአዊ እርዳታ ያለማግኘታቸውን እና በዚህም ቀደም ብሎ የነበረው የሰብአዊ ቀውስ በከፍተኛ ሁኔታ የተባባሰ መሆኑን ተመልክቷል። ኮሚሽኑ በክትትሉ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት እና አረጋውያን በከፍተኛ ሁኔታ ተጎጂ መሆናቸውን እንዲሁም በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና ለመከላከል በሚቻሉ በሽታዎች የሞቱ ሰዎች መኖራቸውን ተመልክቷል።
በትግራይ እና ከፍተኛ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው ሌሎች ክልሎች ያለው የከፋ ሰብአዊ ቀውስ የሚፈልገውን አስቸኳይ ምላሽ ለመስጠት መንግሥት እና የሰብአዊ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች እርዳታው ለተገቢው የሕብረተሰብ ክፍል በአግባቡ መድረሱን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ዝግጅቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ በቂ፣ ወቅቱን የጠበቀ እና ልዩ ፍላጎቶች ያሏቸውን ወይም ለመብቶች ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ፍላጎትን ታሳቢ ያደረገ የሰብአዊ ድጋፍ በፍጥነት መልሰው እንዲጀምሩ ኢሰመኮ ያሳስባል።