ለጄኔቫ ስምምነቶች የወል ድንጋጌ የሆነው አንቀጽ 3፣ አስፈላጊ እና በማናቸውም ምክንያት ሊጣሱ ወይም ሊገደቡ የማይችሉ ደንቦችን ይዟል፡፡ ይህ አንቀጽ ሁሉንም የግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች በውጊያ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሌላቸውን ሰዎች እንዲሁም በጠላት ኃይል ቁጥጥር ሥር የሆኑ (በውጊያ ውስጥ መሳተፋቸው የቀረ) ሰዎችን ቢያንስ ያለ ምንም አሉታዊ ልዩነት በሰብአዊነት መያዝን እንዲያከብሩ ያስገድዳል፡፡
በተለይም ከሌሎች ግዴታዎች በተጨማሪ ድንጋጌው፡-
- በተለይም ግድያ፣ አካል ማጉደል፣ ማሰቃየት፣ በእገታ መውሰድ፣ እንዲሁም ጭካኔ የተሞላበት እና አዋራጅ አያያዞችን ይከለክላል፤
- የቆሰሉ እና የታመሙ ሰዎች እንዲሰበሰቡና እንክብካቤ እንዲደረግላቸውም ግዴታ ይጥላል፡፡