ኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም. የአፍሪካ ሕብረት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ ስምምነት (የካምፓላ ስምምነት) መቀበሏን ተከትሎ በወጣው ማጽደቂያ አዋጅ ቁጥር 1187/2020 እንደተመለከተው፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ማለት “በጦርነት፣ በመጠነ ሰፊ ብጥብጦች፣ በሰብአዊ መብት ጥሰቶች ወይም ሰው ሠራሽ ወይም በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ወይም በሚያስከትሏቸው ውጤቶች የተነሳ ከሚኖሩባቸው ቤቶች ወይም መደበኛ የመኖሪያ ቦታዎች እንዲሸሹ ወይም ለቅቀው እንዲወጡ የተገደዱ ነገር ግን የዓለም አቀፍ አውቅና ያለው የሀገር ድንበር ተሻግረው ያልተሰደዱ ሰዎች ወይም ቡድኖች ማለት ነው።”
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር 1.8 ሚልዮን የደረሰ በመሆኑ፤ ኢትዮጵያ በርካታ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ካላቸው ሀገራት አንዷ ነች። የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሀገሪቱ ዜጋ እንደ መሆናቸው፣ የፖለቲካ ተሳትፎ መብታቸው በተለይም የመምረጥና መመረጥ መብታቸውም ሆነ ሌሎች ሰብአዊ መብቶቻቸው ሁሉ የተጠበቁ ናቸው ።
አንድ ምርጫ ሁሉን አቀፍና ፍትሃዊ ከሚያሰኘው መስፈርቶች አንዱ፣ ለሰብአዊ መብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ጨምሮ ለዜጎች ሁሉ አሳታፊ መሆኑ ነው ። በሌላ በኩል የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በምርጫ ሂደት መሳተፍ፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ወደ መደበኛ ቀያቸው በመመለስ ወይም ተፈናቅለው ከሚገኙበት አካባቢ ማኅበረሰብ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲገነቡ እና እንዲቀላቀሉ በማድረግ እና ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሄ በማፈላለግ ሂደት ላይ ጠቃሚ አስተዋጾ አለው።