የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መንገዶች እና ሕንፃዎች ለአካል ጉዳተኞች ያላቸውን የተደራሽነት ሁኔታ አስመልክቶ ስልታዊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምርመራ አካል የሆነ ግልጽ የአቤቱታ መቀበያ (public hearing) መድረክ ሚያዝያ 20 እና 21 ቀን 2018 ዓ.ም. በሃዋሳ ከተማ አካሂዷል። መድረኩ የመንገዶች፣ የሕንፃዎች እና የሕዝብ አገልግሎቶች ተደራሽ አለመሆን አካል ጉዳተኞች ላይ በሚያሳድረው ተጽዕኖ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። ግልጽ የአቤቱታ መቀበያ መድረኩ ኢሰመኮ ታኀሣሥ 17 እና 18 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ካካሄደውና ትኩረቱን በሕንፃዎች ተደራሽነት ላይ ያደረገው ይፋዊ የአቤቱታ ምርመራ መድረክ የቀጠለ ነው።
በመድረኩ ኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ደርሶብናል ካሉ 24 ተጎጂዎች (18 ወንዶች እና 6 ሴቶች) የቀረቡ ከ70 በላይ አቤቱታዎችን አድምጧል። ከአቤቱታ አቅራቢዎች መካከል 7ቱ ዐይነ ሥውራን፣ 15ቱ አካላዊ ጉዳት ያለባቸው እንዲሁም 2ቱ መስማት የተሳናቸው ናቸው። በመድረኩ 19 ተጎጂዎች ጉዳያቸውን በአካል በመገኘት ያቀረቡ ሲሆን፤ የአንድ ተጎጂ ጉዳይ በሚስጥር ተደምጧል። በተጨማሪም 4 ተጎጂዎች ጉዳያቸውን በተወካዮቻቸው በኩል አቅርበዋል።
ግልጽ የአቤቱታ ምርመራ መድረኩ በኢትዮጵያ መንገዶች እና ሕንፃዎች ለአካል ጉዳተኞች ያላቸው ተደራሽነት አሁንም አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ሆኖ መቀጠሉን አመላክቷል። የተደራሽነት ችግር አካል ጉዳተኞች እንደ ጤና፣ ትምህርት፣ ሥራ፣ በሕዝብ አገልግሎቶች የእኩል ተጠቃሚነት መብት፣ የመንቀሳቀስ ነፃነት እና በባህላዊ ሕይወት ውስጥ የመሳተፍ መብትን የመሳሰሉ መሠረታዊ መብቶቻቸውን የመጠቀም ዐቅማቸውን በከፍተኛ ደረጃ ይገድባል። በተጨማሪም አካል ጉዳተኞችን አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ደኅንነታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ነው።
የኢሰመኮ ስልታዊ ምርመራ እነዚህ ተግዳሮቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መዋቅራዊ በሆኑ መልኩ ተደጋጋሚ እና ሰፊ ይዘት ያላቸው መሆናቸውን ተከትሎ የተካሄደ ነው። ይህ የምርመራ ሂደት ወጥ የሆኑ የመብት ጥሰት ሁኔታዎች እና ዝንባሌዎችን፣ እንዲሁም ተደጋጋሚ ጥሰቶች እንዲከሰቱ የሚያደርጉ መዋቅራዊ መንስኤዎችን ለመመርመር የሚረዳ ሲሆን፤ ዓላማውም ችግሮችን በመለየት ዘላቂ መፍትሄዎችን ማቅረብ ነው። ይፋዊ የሕዝብ አቤቱታ መቀበያ መድረኮችም ተጎጂዎች ጉዳያቸውን በቀጥታ ለባለድርሻ አካላት፣ ለሚመለከታቸው የመንግሥት እና መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት እንዲያቀርቡ በማድረግየሂደቱ አካል እንዲሆኑ የሚያስችል ነው።
በመድረኩ ላይ ምስክርነታቸውን የሰጡ ተጎጂዎች፣ ተደራሽ ያልሆኑ መንገዶችና ሕንፃዎች ለዕለት ከዕለት ሕይወታቸው እንቅፋት መሆናቸውንና መብቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ እንዳይጠቀሙተግዳሮት እንደሆኑባቸው ገልጸዋል። የጤና አገልግሎት፣ ትምህርት፣ ሥራ እና የሕዝብ አገልግሎቶችን በማግኘት ረገድ ያሉባቸውን ተግዳሮቶች እንዲሁም ተደራሽ ባልሆኑ መሠረተ ልማቶች ምክንያት የሚደርሱባቸውን ከባድ የደኅንነት ስጋቶችንም አጉልተው አሳይተዋል። በተለይም በኢትዮ ቴሌኮም፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና በሌሎች አካላት በሚከናወኑ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ላይ ተገቢው የጥንቃቄ ምልክት ሳይደረግላቸው ክፍት ሆነው የሚቀሩ የፍሳሽ ማስወገጃዎች ከፍተኛ ስጋት እየፈጠሩ መሆናቸውን አንስተዋል።
ተጎጂዎቹ አክለውም፣ በጤና ተቋማት ውስጥ ያሉ ተደራሽ ያልሆኑ መጸዳጃ ቤቶችና የተቋማቱ መግቢያዎች አካል ጉዳተኞች የሕክምና ዕርዳታ ለማግኘት በሚሄዱበት ወቅት ችግር እንደሚፈጥሩባቸውና በታመሙ ጊዜም ለእንግልት እንደሚዳርጓቸው ገልጸዋል። በተለይም ሴት አካል ጉዳተኞች በእርግዝና እና በወሊድ ወቅት የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች በማንሳት ምስክርነታቸውን የሰጡ ሲሆን፤ አመቺ ሁኔታዎች ባለመኖራቸው ምክንያት በጤና ተቋማት ውስጥ ሰብአዊ ክብርን የሚነኩ ሁኔታዎች እንደሚገጥሟቸው አስረድተዋል።
በተጨማሪም፣ የትምህርት ተቋማት ተደራሽ አለመሆን አካል ጉዳተኞች በትምህርት ራሳቸውን የማብቃት እና በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ውስጥ ሙሉ በሙሉ የመሳተፍ ዕድላቸውን የሚያሳጣ ዋነኛ እንቅፋት ተደርጎ ተጠቅሷል። በተመሳሳይ፣ ተደራሽ ያልሆኑ የሥራ ቦታዎች በርካታ አካል ጉዳተኞችን ከመደበኛ የሥራ ዕድል ማግለላቸውን የቀጠሉ ሲሆን፤ ይህም ኢ መደበኛ የሥራ ዘርፍ ውስጥ እንዲሠማሩ፣ ለሥራ አጥነት እንዲሁም ለጥገኝነት ዳርጓቸዋል። ተጎጂዎቹ አክለውም፣ ተደራሽ ያልሆኑ የሕዝብ ተቋማት እንደ ባንክ ያሉ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት በሌሎች ሰዎች ዕርዳታ ላይ እንዲደገፉ እንዳስገደዳቸው ገልጸዋል።
በግልጽ የአቤቱታ ምርመራ መድረኩ ላይ አቤቱታ የቀረበባቸው በአጠቃላይ 23 ተቋማት እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግሥት ባለድርሻ አካላት በምላሽ ሰጪነት የተሳተፉ ሲሆን፤ በተቋሞቻቸው ላይ የተነሱትን በርካታ ስጋቶችና ቅሬታዎች አምነው ተቀብለዋል። ለአካል ጉዳተኞች የመንገዶችና የሕንፃዎችን ተደራሽነት ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆኑ ማሻሻያዎችን ለማድረግም ቃል ገብተዋል። በተጨማሪም፣ ተቋማቱ ከሚመለከታቸው የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ጋር በትብብር ለመሥራት እና የተደራሽነት ደረጃዎች (accessibility standards) ተፈጻሚነትን ለማረጋገጥ ቃል ገብተዋል። በግንባታ ፈቃድ፣ በቁጥጥር እና በክትትል ላይ ኃላፊነት ያለባቸው ባለሥልጣናት በበኩላቸው የማስፈጸሚያ እና የክትትል ሥርዓቶችን ለማጠናከር ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል።
መንገዶችና ሕንፃዎች ለአገልግሎት ክፍት ከመደረጋቸው በፊት ከብሔራዊ እና ዓለም አቀፍ የሕግ ደረጃዎችን መሠረት ባደረገ መልኩ ሊቀረጹ፣ ሊገነቡና ቁጥጥር ሊደረግባቸው ይገባል። የጤና ተቋማት፣ ባንኮች፣ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ሌሎች የመንግሥትና የግል ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ሙሉ በሙሉ ተደራሽ መሆናቸውን የማረጋገጥና ሁሉን አቀፍ አገልግሎቶችን የመስጠት ግዴታ ያለባቸው ሲሆን፤ ከተደራሽነት ጋር በተያያዙ ውሳኔዎች ላይም የእነሱን አስተያየት ትርጉም ባለው መልኩ ማካተት ይኖርባቸዋል።
ኢሰመኮ ሁሉም አቤቱታ የቀረበባቸው ተቋማት የተሰጡትን ምክረ ሐሳቦች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲያደርጉ በጥብቅ ያሳስባል። በተጨማሪም፣ የሕንፃ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣናት በእነዚህ ተቋማት አማካኝነት የምክረ ሐሳቦቹን አፈጻጸም ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲከታተሉና መተግበራቸውን እንዲያረጋግጡ ጥሪ ያቀርባል።
የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል በኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አካል ጉዳተኞች ለዕለት ከዕለት ሕይወታቸው አስፈላጊ የሆኑ ሕንፃዎችና መንገዶች ተደራሽ ባለመሆናቸው ምክንያት አሁንም ለከፋ ችግር ተጋልጠው ይገኛሉ ብለዋል። በዚህም ምክንያት የጤና፣ የትምህርት፣ የሥራ፣ በሕዝብ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም፣ የነጻነት እና የክብር መብቶቻቸውን በዕለት ከዕለት ሕይወታቸው ሙሉ በሙሉ ማግኘት አልቻሉም። አክለውም መሠረተ ልማቶች በከፍተኛ ወጪ የሚገነቡ በመሆናቸው ያለምንም ልዩነት ለሁሉም ተደራሽ መሆን እንዳለባቸው አጽንዖት ሰጥተዋል። ዶ/ር አብዲ ተደራሽ የሆኑ ሕንፃዎችን የሚገነቡ ተቋማትን ዕውቅና መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ የዕለት ከዕለት ሕይወት ተሞክሯቸውን በግልጽ መድረኩ ላካፈሉ ተጎጂዎች፣ እንዲሁም የማስተካከያ እርምጃዎችን ለመውሰድና ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት ቁርጠኝነታቸውን ላሳዩ ምላሽ ሰጪ ተቋማት ምስጋና አቅርበዋል።