የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የመደራጀት ነጻነትን አስመልክቶ መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል። በውይይት ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ከክልል ፍትሕ ቢሮዎች፣ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን፣ ከኢትዮጵያ የሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን፣ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የተወጣጡ ተወካዮች እና ጋዜጠኞች ተሳትፈዋል።

በውይይቱ የመደራጀት ነጻነትን የሚመለከቱ ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ሀገር አቀፍ የሕግ ማዕቀፎች እንዲሁም ኢሰመኮ መብቱን አስመልክቶ በአዲስ አበባ ከተማ እና በአማራ፣ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ሶማሊ እና ትግራይ ክልሎች ባከናወናቸው ክትትሎች የተለዩ ግኝቶች ቀርበው ሰፊ የሐሳብ ልውውጥ ተደርጎባቸዋል።

በውይይቱ ሠራተኞች ስለመደራጀት መብት ያላቸው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን ተደራጅተው መብቶቻቸውን እንዳይጠይቁ እክል መፍጠሩ፤ መብታቸውን በሚጠይቁ ሠራተኞች ላይ ከሥራ ማባረር ጀምሮ የተለያዩ አስተዳደራዊ ጫናዎች የሚደርሱባቸው መሆኑ እንዲሁም በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ የሚተላለፉ እገዳዎች በመደራጀት ነጻነት እና በሲቪል ምኅዳሩ ላይ የፈጠሩት አሉታዊ ተጽዕኖ በአሳሳቢነት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች የመደራጀት ነጻነት በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ጥበቃ ከተደረገላቸው መሠረታዊ መብቶች መካከል አንዱ መሆኑንና ማንኛውም ሰው ሕጋዊ ለሆነ ማንኛውም ዓላማ በማኅበር የመደራጀት መብት እንዳለው የተደነገገ በመሆኑ ለተፈጻሚነቱ ምቹ የሕግ እና የአሠራር ማዕቀፎችን መፍጠር እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተዋል።

የኢሰመኮ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር መቅደስ አመኑ የመደራጀት ነጻነት የዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ መሠረት በመሆኑ መንግሥት በተለይም በምርጫ ዐውድ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እጩዎች፣ መራጮች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በነጻነት እንዲደራጁ እና እንዲሠሩ አስቻይ ሁኔታዎችን ሊፈጥር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ አክለውም የመደራጀት መብት ሊገደብ የሚችለው በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች መሠረት በሕግ የተደነገገ፣ አስፈላጊ እና ተመጣጣኝ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ሊሆን እንደሚገባ እና ለዚህም ተፈጻሚነት ሁሉም አካላት በቅንጅት መሥራት እንደሚገባቸው አስረድተዋል፡፡