የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከ‘ፕሮጀክት ኤክስፔዳይት ጀስቲስ’ (Project Expedite Justice (PEJ)) ጋር በመተባበር፣ በኢሰመኮ እና ሲቪል ማኅበራት የክልል የትብብር መድረክ ሥር ለሚገኙ አባላት በሰብአዊ መብቶች ክትትልና ውትወታ ላይ ያተኮረ የዐቅም ግንባታ ሥልጠና ከመጋቢት 14 እስከ 17 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ ሰጥቷል። የስልጠናው ዋና ዓላማ በክልል ደረጃ የሚገኙ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በተሻለ መልኩ ለመከታተልና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዐቅም መገንባት ነው።



በስልጠናው ከአፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች የተውጣጡ 28 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተሳትፈዋል፡፡
በስልጠናው የሰብአዊ መብቶች ክትትል መሠረታዊ መርሖችና ሥነ-ምግባር፣ የክትትል ዘዴዎች፣ መረጃና ማስረጃ ማሰባሰብ፣ ማረጋገጥ እና ሰነድ አያያዝ፣ ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ የሕግ ማዕቀፎች፣ ግልጽ የመረጃ ምንጮችን (Open Source Information) ለተገቢው ሥራ መጠቀም፣ የመረጃዎችን ትክክለኛነት ማረጋገጥ እንዲሁም መረጃዎችን ከሕግ አንጻር መተንተንና ሪፖርት ማድረግን የተመለከቱ ዝርዝርዝ ጉዳዮች ቀርበዋል። እነዚህም የክትትል ግኝቶችን ተዓማኒነት ለማረጋገጥና በግኝቶቹ ላይ ተመሥርቶ ውጤታማ የሰብአዊ መብቶች ውትወታ ስልቶችን ለመንደፍ የሚያስችሉ መሆናቸው ተመላክቷል።



ስልጠናው የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የቅድመ-ማስጠንቀቂያ ሥርዓትን በመዘርጋት፣ የፈጣን ምላሽ አሰጣጥ ክህሎቶችን በማጠናከር እና ለተጎጂዎች ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ በየክልላቸው የሚታዩ የሰብአዊ መብቶች ስጋቶችን ቀድሞ በማሳወቅና አስቸኳይ ምላሽ በሚሹ ጉዳዮች ላይ በቅንጅት በመሥራት ረገድ ያላቸውን ሚና እንደሚያጠናክር ተገልጿል።

የኢሰመኮ የፕሮግራምና የአጋርነት ሥራ ክፍል ከፍተኛ ዳይሬክተር ማንያውቃል መኮንን በስልጠናው የተሳተፉ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር በመለወጥ በሰብአዊ መብቶች ጥበቃና ውትወታ ሥራዎች ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።