ሕፃናት የሚባሉት እነማን ናቸው?

የሕፃናት መብቶች ስምምነት (Convention on the Rights of the Child) እና የአፍሪካ የሕፃናት መብቶች እና ደኅንነት ቻርተር (African Charter on the Rights and Welfare of the Child) ከ18 ዓመት በታች የሆነ ማንኛውም ሰው ሕፃን እንደሚባል ይደነግጋሉ።1 የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 36 የሕፃናት መብቶችን የደነገገ ቢሆንም የሕፃናትን የዕድሜ ወሰን በግልጽ አያስቀምጥም። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከላይ የተጠቀሱትን የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ያጸደቀች በመሆኗ እና በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 9 (4) መሠረት ሀገሪቱ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ ሕግ አካል በመሆናቸው እንዲሁም የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 13 (2) በሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ ሦስት የተደነገጉት መሠረታዊ መብቶችና ነጻነቶች ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግጋት፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶችና ሰነዶች መርሖች ጋር በተጣጣመ ሁኔታ መተርጎም እንዳለባቸው ስለሚደነግግ፣ በኢትዮጵያም ሕፃን የሚባለው ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች የሆነ ማንኛውም ሰው ነው የሚለው ትርጓሜ ተቀባይነት ያለው ይሆናል።

የሽግግር ፍትሕ ሂደት እና የሕፃናት መብቶች ግንኙነት ምንድን ነው?

የሽግግር ፍትሕ ማኅበረሰቦች ያለፉ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን፣ ክፍፍሎችን እና አለመመጣጠኖችን ለማስወገድ፤ ተጠያቂነትን፣ ፍትሕን እና ዕርቅን በማረጋገጥ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ወደ ሆነ አዲስ ምዕራፍ ለመሸጋገር የሚያከናውኗቸውን መደበኛ እና መደበኛ ያልሆኑ ተግባራት እና ሂደቶች ያጠቃልላል።

ሁሉን-አቀፍ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት አራት እርስ በርስ የተያያዙ እና የሚደጋገፉ መሠረታዊ ስልቶችን በውስጡ የያዘ ሲሆን እነዚህም፦

  1. እውነትን ማፈላለግ እና ይፋ ማውጣት፤
  2. ተጠያቂነትን ማስፈን፤
  3. ለተጎጂዎች ማካካሻ መስጠት እና
  4. ተቋማዊ ማሻሻያዎችን ማድረግን ጨምሮ በማኅበረሰባዊ እና ባሕላዊ ዘርፎች የሚወሰዱ እርምጃዎችን በመተግበር ጥሰቶች ድጋሚ እንዳይከሰቱ ዋስትና መስጠት ናቸው።

በትጥቅ ግጭቶች ወይም ጨቋኝ በሆኑ ሥርዓቶች በሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ዐውድ ውስጥ ሕፃናት ለሞት፣ አካላዊ ጉዳት፣ የሥነ-ልቦና ቀውስ፣ መፈናቀል፣ ጾታዊ ጥቃት፣ የግዳጅ ምልመላን ጨምሮ ሕገ-ወጥ ምልመላ እና ለሌሎችም የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ይሆናሉ። ከዚህም በተጨማሪ ጥሰቶች በቤተሰቦቻቸው፣ በአካባቢያቸው ማኅበረሰብ አባላት፣ በጓደኞቻቸው እና በሌሎችም ሰዎች ላይ ሲፈጸሙ ይመለከታሉ፤ ወይም ሕፃናት ራሳቸው በሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ውስጥ በተለያየ መልኩ ተሳታፊ ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህ ምክንያት ሕፃናት በሽግግር ፍትሕ ሂደቶች ውስጥ የተጎጂነት፣ የምስክርነት እና/ወይም የተጠርጣሪነት ስፍራ ሊኖራቸው የሚችል ሲሆን፣ በእነዚህ ሂደቶች ሁሉ ውስጥ የሚያልፉበት የተሳትፎ ሁኔታ ተጋላጭነታቸውን ከግንዛቤ ያስገባ እና ሰብአዊ መብቶቻቸውን ያከበረ መሆን አለበት።

በሽግግር ፍትሕ ሂደት ለሕፃናት መብቶች ሊደረግ የሚገባውን ጥበቃ የሚደነግጉ የሰብአዊ መብቶች ማዕቀፎች የትኞቹ ናቸው?

የሽግግር ፍትሕ ከሕፃናት ፍትሕ የማግኘት መብት፣ ከሕፃናት መብቶችና ጥቅሞች ቀዳሚነት መርሕ (the best interest of the child)፣ ከሕፃናት የተሳትፎ፣ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ እና የመሰማት መብቶች ወዘተ. ጋር ቁርኝት ያለው ስለሆነ፣ በሂደቶቹ ውስጥ ሊደረግላቸው የሚገባው ጥበቃ እነዚህን እና ሌሎች ተያያዥ የሕፃናት መብቶችን ከሚደነግጉ ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ሕጎች አንጻር ሊታይ ይችላል።

ዓለም አቀፉ የሕፃናት መብቶች ስምምነት፣ የአፍሪካ የሕፃናት መብቶች እና ደኅንነት ቻርተር እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሕፃናትን በሚመለከቱ ማናቸውም ጉዳዮች ላይ የሕፃናት ጥቅምና መብት ቀዳሚ ሊሆን እንደሚገባ ደንግገዋል።3 ሕፃናት በሚመለከቷቸው ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ ሐሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ እና የመሰማት መብት ያላቸው ሲሆን፤4 ይህም በዳኝነት፣ በአስተዳደር እና ሌሎች የሥልጣን አካላት በሕፃናት ላይ በሚወሰኑ ጉዳዮች ላይ ሕፃናት በቀጥታ ወይም በተወካዮቻቸው አማካይነት ለመሳተፍ እና ሐሳባቸውን ለመግለጽ ያላቸውን መብት እንዲሁም ዕድሜያቸውንና የአእምሮ ብስለታቸውን ባገናዘበ መልኩ ለአስተያየታቸው ተገቢው ክብደት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ይጨምራል።

ሕፃናትን በተጎጂነት፣ በምስክርነት ወይም በተጠያቂነት በሚያሳትፉ የፍትሕ ሂደቶች ሊረጋገጡ የሚገቡ መሠረታዊ ጥበቃዎችን በማስመልከት በተባበሩት መንግሥታት እና በአፍሪካ ኅብረት ደረጃ የወጡ ልዩ ልዩ ሰነዶች በሽግግር ፍትሕ ሂደት ዐውድ ጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ መርሖችን እና መመዘኛዎችን አካትተዋል።5 በሌላ በኩል የሽግግር ፍትሕን አስመልክቶ የተ.መ.ድ.ን አካሄድ ለመግለጽ እ.ኤ.አ. መጋቢት 2010 የወጣው የተ.መ.ድ. ዋና ጸሐፊ የመመሪያ ማስታወሻ (Guidance note of the United Nations Secretary General: United Nations Approach to Transitional Justice) እንዲሁም እ.ኤ.አ. ጥቅምት 2023 የወጣው በሽግግር ፍትሕ ላይ የዋና ጸሐፊው መመሪያ ማስታወሻ (Guidance Note of the Secretary General on Transitional Justice) የሕፃናትን ሁኔታና ፍላጎቶች ያከበረ የሽግግር ፍትሕን (child-sensitive TJ) በመርሕነት በማስቀመጥ ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች ይዘረዝራሉ።

የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ እና በሚያዝያ ወር 2016 ዓ.ም. የጸደቀው የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ እንደዚሁ በሽግግር ፍትሕ ሂደት ሕፃናት በሚገባ ሊካተቱ እንደሚገባ በማመላከት፣ እውነትን በማፈላለግ እና ይፋ በማውጣት፣ ተጠያቂነትን በማስፈን፣ ለተጎጂዎች ማካካሻ በመስጠት እንዲሁም ተቋማዊ ማሻሻያዎችን ማድረግን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ጥሰቶች ድጋሚ እንዳይከሰቱ ዋስትና በመስጠት ረገድ ከሕፃናት መብቶች አንጻር ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች የሚመለከቱ ዝርዝር ድንጋጌዎች እና መርሖዎችን ይዘዋል።

ኢሰመኮን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻዎች በዝግጅቱ የተሳተፉበት በሽግግር ፍትሕ ሂደት የተጎጂዎች እና ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፎ ስትራቴጂ በረቂቅ ደረጃ የሚገኝ ሲሆን ሕፃናት በሽግግር ፍትሕ ሂደት ልዩ ልዩ ምዕራፎች ሊከበሩላቸው የሚገቡ መብቶችን መሠረት ያደረጉ ዝርዝር ስልቶችና ተግባራትን አካትቶ ወደሥራ እንደሚገባ ይጠበቃል።

የሕፃናትን መብቶች ያከበረ የሽግግር ፍትሕ ሂደትን ለማረጋገጥ ምን እርምጃዎችን መውሰድ ይገባል?

ከላይ የተጠቀሱት ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ማዕቀፎች እውነትን በማፈላለግ እና ይፋ በማውጣት፣ ተጠያቂነትን በማስፈን፣ ለተጎጂዎች ማካካሻ በመስጠት እንዲሁም ጥሰቶች ድጋሚ እንዳይከሰቱ የሕግና የተቋም ማሻሻያ በማድረግ ዋስትና በመስጠት ምዕራፎች ሁሉ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ሰብአዊ መብቶች ተኮር እና ተጎጂዎችን ማእከል ያደረገ መሆን እንዳለበት በመደንገግ፣ በተለይም ከሕፃናት መብቶች አንጻር አግባብነት ያላቸውን መርሖች እና መመዘኛዎች ያስቀምጣሉ።

በዚሁ መሠረት መንግሥትን ጨምሮ በሽግግር ፍትሕ ሂደት ተሳትፎ የሚያደርጉ ባለድርሻዎች ሊወስዷቸው ከሚገቡ በርካታ ቁልፍ እርምጃዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።

የሕፃናትን ከፍተኛ ተጋላጭነት ከግንዛቤ ማስገባት፦ ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የመለየትና ዕውቅና የመስጠት፣ ፍትሕን የማረጋገጥ እንዲሁም ድጋሚ እንደማይፈጸሙ ዋስትና የመስጠት ጥረቶች የሕፃናትን ከፍተኛ ተጋላጭነት ያገናዘቡ እና ተጋላጭነታቸውን በዘላቂነት ለመቀነስ የሚያስችሉ ውጤታማ እርምጃዎችን ያካተቱ መሆን አለባቸው። ይህም ለምሳሌ ጾታዊ ጥቃቶችን ጨምሮ በሕፃናት ላይ የተፈጸሙ ጉልህ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ የተሟላ ምርመራ እና የወንጀል ተጠያቂነትን ማረጋገጥን ይጨምራል።

የሕፃናትን የተሟላ ተሳትፎ ማረጋገጥ፦ ሕፃናት በሽግግር ፍትሕ ሂደቶች እንደ ተጎጂ ብቻ ሳይሆን እንደ ቁልፍ የመፍትሔ አካል መቆጠር ይገባቸዋል፤ ስለዚህም ለምሳሌ እውነትን በማፈላለግ እና የወንጀል ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ሂደቶች ውስጥ እንደ ተጎጂ ሊኖራቸው ከሚገባው ትርጉም ያለው ተሳትፎ ባሻገር የሽግግር ፍትሕ ሂደቶችን በመቅረጽ፣ በመተግበር እና በመገምገም ምዕራፎች ሁሉ የመሳተፍ እና የመሰማት መብታቸው መከበሩ ሊረጋገጥ ይገባል። በዚህ ረገድ የሕፃናትን ተሳትፎ ሊገድቡ የሚችሉ ባሕላዊ እና ማኅበራዊ አሠራሮችን እና መዋቅሮችን መለየት እና አስቻይ የመፍትሔ እርምጃዎችን መተግበር ያስፈልጋል።

ለሕፃናት ምቹ የሆኑ (child friendly) ሁኔታዎችና ሥነ-ሥርዓቶችን ማካተት:- በሽግግር ፍትሕ ሂደቶች የሕፃናትን ውጤታማ ተሳትፎ እና ጥበቃ ለማረጋገጥ አስቻይ መሠረተ ልማቶችን፣ የሰው ኃይል (ለምሳሌ በሕፃናት መብቶች ጥበቃ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን) እንዲሁም የሥነ-ሥርዓት አማራጮችን ማሟላት ያስፈልጋል። ይህም ለምሳሌ ለሕፃናት ተስማሚ የሆኑ እና ምስጢራዊነታቸው የተጠበቁ የተለዩ የእውነት ማፈላለግ ወይም የክስ አሰማም ሂደቶችን ማመቻቸትን ይጨምራል።

የሕፃናት ጥቅምና መብት ቀዳሚነት (the best interest of the child):- በሽግግር ፍትሕ ሂደቶች የሚወሰዱ እርምጃዎች ለሕፃናት መብቶችና ጥቅሞች ቅድሚያ የመስጠት መርሕን መሠረት ማድረግ አለባቸው። በሂደቱ የሚያልፉ ሕፃናትን ማንነት በምስጢር መያዝ (anonymity)፣ በግዳጅ ምልመላ ሳቢያ በሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ የተደረጉ ሕፃናትን እንደ ጥፋት ፈጻሚ ብቻ ሳይሆን እንደ ተጎጂ መቁጠር፣ ለመሰል ሕፃናት ከዳኝነት ሂደቶች ውጪ ያሉ አማራጭ የተጠያቂነት ሂደቶች ጥቅም ላይ የሚውሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት፤ በማካካሻ እና የማሻሻያ እርምጃዎች (reform measures) የሕፃናትን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳቶች እና ተጋላጭነት ዘላቂ ምላሽ የሚሰጡ ውጤታማ እርምጃዎችን ማካተት እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጎጂ የሆኑ ሕፃናት ዐቅማቸውን መልሶ ለመገንባት የሚያስችሉ የትምህርት፣ የሕክምናና የሥነ ልቦና አገልግሎቶችን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ማድረግ ለሕፃናት መብቶችና ጥቅሞች ቅድሚያ ከመስጠት መርሕ ጋር በተያያዘ በሽግግር ፍትሕ ማዕቀፎች ከተመላከቱ ጠቃሚ አማራጮች መካከል ናቸው።

ድርብርብ ተጋላጭነት ላለባቸው ሕፃናት ትኩረት መስጠት፦ የሽግግር ፍትሕ ስልቶች እና ሂደቶች ሴት፣ አካል ጉዳተኛ፣ ተፈናቃይ እና በግጭቶች ውስጥ በተለያየ መንገድ ተሳትፎ የነበራቸው ሕፃናት የሚገኙበትን የድርብርብ ተጋላጭነት ሁኔታ ያገናዘቡ መሆን አለባቸው።

በሂደቱ ለሚያልፉ ሕፃናት ድጋፍ እና ጥበቃ ማድረግ፦ ሂደቱ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ሕፃናት የሕግ፣ የጤና፣ የሥነ-ልቦና እና ማኅበራዊ ድጋፍ እና ክትትል ማግኘታቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። በተለይም ተጎጂ ሕፃናት ለደረሰባቸው አካላዊ፣ ጾታዊ፣ ወሲባዊ ወዘተ. ጥቃቶች መፍትሔ ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት በማኅበረሰቡ፣ በአገልግሎት ሰጪ ሰዎች ወይም በተቋማት ተጨማሪ ጉዳትና ጥቃት (ሁለተኛ ደረጃ ጥቃት) እንዳይደርስባቸው፤ የጥቃት ሰለባ ሕፃናትን ከመውቀስ፣ የደረሰባቸውን ጉዳት ከማሳነስ፣ ሕፃናትን በተደጋጋሚ ከመጠየቅ ወይም ከመጠራጠር (ተገቢውን እምነት አለማሳደር)፣ ለሕዝብ ከማጋለጥ (public exposure)፣ ከማግለልና አድልዎ እንዲሁም ከቸልታ (ተገቢውን ትኩረት፣ ጥበቃና ድጋፍ ከመንፈግ) የጸዱ የሕግ፣ የተቋም እና የአሠራር ማዕቀፎችን መዘርጋትና መተግበር ይገባል።