በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት በአምስት ከተሞች ከታኅሣሥ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል የመዝጊያ ዝግጅት በታኅሣሥ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተካሄደ፡፡
ሰብአዊ ክብር፣ ነጻነት እና ፍትሕ ለሁሉም በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ በአዳማ፣ በአዲስ አበባ፣ በባሕር ዳር፣ በሃዋሳ እና በጅግጅጋ በተካሄደው የፊልም ፌስቲቫል 15 በሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥኑ አዳዲስ እና ከዚህ በፊት ለዕይታ የቀረቡ በዓለም አቀፍ መድረኮች ጭምር ተቀባይነትን ያተረፉ የሙሉ ጊዜ እና አጫጭር ፊልሞች እንዲሁም ዘጋቢ ፊልሞች ለዕይታ እና ለውይይት ቀርበዋል። በፌስቲቫሉ ላይ የፊልም እና በሌሎች የኪነጥበብ ዘርፍ ሙያ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች እና ተማሪዎችን ጨምሮ በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።
አዲስ አበባ በተካሄደው የፌስቲቫሉ የመዝጊያ ዝግጅት ላይ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ባደረጉት ንግግር፤ “ሰብአዊ ክብር፣ ነጻነት እና ፍትሕ ለሁሉም” የሚለው የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን መሪ ቃል ሁላችንንም ወደ ሰብአዊ መብቶች መሰረታዊ ነጥቦች መልሶናል ብለዋል። አክለውም የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ከኪነጥበብ ዘርፉ ጋር ግንኙነት በመፍጠር እነዚህን መሰል ፌስቲቫሎች የሚያዘጋጁት በሥነ ጥበብ እና በኪነ ጥበብ ሥራዎች የሚተላለፉ መልእክቶች እንዲሁም ባለሞያ ያልሆንነው ሌሎች ሰዎች ስለምናስተላልፋቸው መልእክቶች በታሰበበት እና በታቀደበት መልኩ እንድንጠነቀቅ ለማስታወስ ነው በማለት አስረድተዋል።
በየዓመቱ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀንን ለማሰብ በኢሰመኮ አዘጋጅነት የተጀመረው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል፤ በቀጣይ ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ለሦስተኛ ዙር የሚመለስ ይሆናል።