በአሁኑ ወቅት ትምህርት ቤቶች ለአዲሱ ዓመት ተመልሰው በሚከፈቱበት ወቅት ላይ ብንሆንም በርካታ ሕፃናት እና ታዳጊዎች በግጭት፣ በመፈናቀል፣ በድርቅ ምክንያት ወይም በኑሮ ውድነት አልያም በሌሎች ችግሮችና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በመሆናቸው ምክንያት ወደ ትምህርት ቤት አይገቡም ወይም አይመለሱም። በጦርነት እና በግጭቶች ሳቢያ የወደሙባቸው ትምህርት ቤቶቻቸው፣ የጤና ተቋማቶቻቸው እና የተቋረጡባቸው መሰረተ ልማቶችና አገልግሎቶች እንዲጠገኑ በመጠበቅ ላይ ያሉ ልጆቻችን በሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው።
ከግማሽ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ18 ዓመት በታች እንደመሆኑ መጠን ይህ የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ በማንኛውም የሥራ ዓይነት እና በተለይም በመንግሥት ሥራ ላይ ባለን ሰዎች ላይ ተጨማሪ እና አፋጣኝ የሆኑ ኃላፊነቶችን የሚጥል ነው።
ከእነዚህ መካከል ዋነኛው በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ያሉ ሕፃናት ሰላም አግኝተውና ደኅንነታቸው ተጠብቆ ለመኖር እንዲችሉ ጥረት ማድረግ እና የተጀመሩ ጥረቶችን በማንኛውም መንገድ መደገፍን የሚመለከተው ነው። ለሀገራችን ሰላም የአቅማችንን የምናደርገው ድጋፍ በቀጥታ ተሳትፎ የምናከናውናቸውና ፍትሕና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ወይም ዘላቂ የመልሶ ማቋቋም ተግባራት እንዲከናወኑ ማድረግ ወይም ለተጎዳ አንድ ቤተሰብ የልጆች ደብተር በመግዛት በግላችን የምናደርገው ድጋፍ ሊሆን ይችላል። አልያም በአካባቢያችን፣ በድረ ገጾች ወይም በሕትመት በምናስተላፋቸው መልእክቶች እና ንግግሮች አማካኝነት ሊሆንም ይችላል።
በአሁኑ ወቅት እኛ እራሳችን ሕፃናት እና ልጆች ከነበርንበት ወቅት በእጅጉ በተለየ መልኩ እያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን በቴክኖሎጂ እና በኢንተርኔት ተቀርጾ የሚቀርና የእኛ ልጆች ለአካለ መጠን ሲደርሱ ፈልገው ማግኘት የሚችሉት መሆኑ ልጆችን እና ታዳጊዎችን በተመለከተ ያለብንን ኃላፊነት ክብደት የሚጨምር ነው። ልጆቻችን አድገው በኢንተርኔት የታሪክ ማኅደር የተናገርነውን እና ያደረግነውን በማየት እንዳይሸማቀቁ፣ ይልቁንም ክብር እና ኩራት እንዲሰማቸው ከማድረግ የበለጠ የሚያስጨንቅ ኃላፊነት ሊኖር አይችልም።
ልጆቻችን ለአካለ መጠን በሚደርሱበት ወቅት ስለሚጠብቃቸው ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ከባቢያዊ ሁኔታ መተንበይ ባይቻልም የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረበት፣ የአየር ለውጥ በሁሉም መልኩ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድርበት፣ በቴክኖሎጂ እድገት አማካኝነት የተለያዩ አዳዲስ ምቾቶችን ማግኘት የሚችሉበት ሆኖም በዚያው ልክ የሥራ ዕድሎች ውስንና አዳዲስ እና ከፍተኛ ደረጃ ክህሎቶችን የሚጠይቁበት እንደሚሆን የታወቀ ነው።
ልጆቻችንን ለዚህ ለመጪው ጊዜ ተወዳዳሪ መሆን እንዳይችሉ ወይም የሌሎች ሀገራት ወጣቶች ከሚጓዙበት የእድገት ፍጥነት እንዲዘገዩ የሚያደርጉ ሁኔታዎችን ለመቅረፍ ገና ብዙ እርምጃዎች፣ ሥራዎች እና ኃላፊነቶች ይጠብቁናል። ትምህርት ቤቶችን የመጠገኑ፣ የመገንባቱ እና ተያያዥ መሰረተ ልማቶችን የማቋቋሙ፣ የትምህርት ጥራትን የማረጋገጡ እንዲሁም ትምህርት ቤቶች ልጆቻችን ለአዕምሮአቸው እድገት ጭምር አስፈላጊ የሆኑትን ንጥረ ነገሮች የያዙ ምግቦችን እና መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን የሚያገኙበት ቦታ እንዲሆኑ ማስቻሉ ዕቅድ፣ ሃብት እና ረዘም ያለ ጊዜ የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል።
ሆኖም በእያንዳንዱ የትምህርት ቤት አስተዳደር፣ መምህራን እና ሠራተኞች እንዲሁም በሚመለከተው የመንግሥት አካል ፍቃድ አማካኝነት እና እገዛ ብቻ፣ ቢያንስ ሀገራችን በምትገኝበት ፈታኝ ጊዜ ውስጥም ጭምር እና በሥራ ላይ ባሉ የትምህርት ተቋማት ውስጥ፣ ትምህርት ቤቶች ልጆቻችን መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶች መርሆችን፣ አብሮ መኖርን እና መዋደድን የሚያዩበትና የሚኖሩበት እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል። ይህ እንዲሆን የትምህርት ተቋማቶች ከአነሳሽ፣ ግጭት ጠንሳሽ ንግግሮች የጸዱ እንዲሆኑ ማድረግ፣ ይልቁንም ተቋማቱ ልጆቻችን ሊሄዱ የሚጓጉበት እና የተሳትፎ፣ የፈጠራና የመዝናኛ ጊዜ የሚያገኙበት፣ እንዲሁም በሥነ ምግባራቸውና በአሠራራቸው ምሳሌ የሚሆኗቸውን ሰዎች የሚያዩበት ቦታ እንዲሆኑ ማድረግ ተጨማሪ ሃብትም ሆነ የተራዘመ ዕቅድ አይጠይቅም።
ስለሆነም፣ በሁሉም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባልደረቦቼ ስም በተቋማችን ላይ የተጣለውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት የአቅማችንን ሁሉ እንደምናደርግ ስገልጽ ለሁሉም ወገኖች ይህንን የሰላም ጥሪ እና መልካም ምኞት በማስተላለፍ ነው።