የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከዴንማርክ የሰብአዊ መብቶች ተቋም (Danish Institute for Human Rights (DIHR)) ጋር በመተባበር “ከንግድና ሰብአዊ መብቶች ጋር የተያያዙ የአውሮፓ ኅብረት የሕግ ማዕቀፎች ለኢትዮጵያ ያላቸው ፋይዳ” በሚል ርዕስ የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረክ መጋቢት 17 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አካሄዷል። ውይይቱ ባለድርሻ አካላት ስለ የአውሮፓ ኅብረት የንግድ ድርጅቶች የዘላቂነት ተገቢ ትጋት መመሪያ (EU Corporate Sustainability Due Diligence Directive (EU CSDDD)) እና የአውሮፓ ኅብረት የግዳጅ ሥራ ክልከላ ደንብ (EU Forced Labour Regulation) ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ እንዲሁም እነዚህ ማእቀፎች በኢትዮጵያ የንግድ ተቋማት እና በሰብአዊ መብቶች አሠራር ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን አንድምታ ለመቃኘት ያለመ ነው።


በውይይቱ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ ከኢትዮጵያ አሠሪዎች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (CEEA) እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብአዊ መብቶች ማእከል የተወጣጡ ኃላፊዎች እና ተወካዮች ተሳትፈዋል።

በመድረኩ፣ አሊስ ሙኔሊ በዴንማርክ የሰብአዊ መብቶች ተቋም የሰብአዊ መብቶች፣ ንግድ እና ቴክኖሎጂ ከፍተኛ አማካሪ የአውሮፓ ኅብረት የንግድ ድርጀቶች የዘላቂነት ተገቢ ትጋት መመሪያ እና የግዳጅ ሥራ ደንብን ዐውድ፣ ዋና ዋና ድንጋጌዎች እና ተጓዳኝ እርምጃዎችን የሚዳስስ ሰፊ ገለጻ አቅርበዋል። በተጨማሪም ውይይቱ የኢትዮጵያ ባለድርሻ አካላት ሊሳተፉባቸው የሚችሉ ስልታዊ መንገዶችን የዳሰሰ ሲሆን፤ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና የሠራተኛ ማኅበራት በአውሮፓ ኅብረት በሚወጡ አዳዲስ ደረጃዎች ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር እንዲሁም እነዚህ ደረጃዎች በኢትዮጵያ ሀገር በቀል የንግድ ተቋማት ላይ ያላቸውን አንደምታ በማሳወቅ ረገድ ያላቸውን ሚና አጽንዖት ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ አሠሪዎች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዳዊት ሞገስ በበኩላቸው፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ የግል ዘርፉ ስለሚገጥሙት ፈተናዎች እና መልካም አጋጣሚዎች ምልከታ ያቀረቡ ሲሆን ስልታዊ ማስተካከያ የሚሹ ጉዳዮችንም ጠቁመዋል። ተሳታፊዎች እነዚህን ደረጃዎች ማሟላት፣ ግንዛቤ ማስጨበጥ እና የተቋማትን እንዲሁም የንግድ ዘርፉን ዐቅም መገንባት ጨምሮ ሁሉን አቀፍ አካሄድ መከተል እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።
የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል በመዝጊያ ንግግራቸው፤ የሀገር ውስጥ የንግድ አሠራሮችን ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ደረጃዎች ጋር ለማጣጣም የጋራ ጥረቶች አስፈላጊ መሆናቸውን አሳስበዋል። ኮሚሽነሩ እነዚህን ጥረቶች ለማገዝ ኢሰመኮ ግንዛቤን በመፍጠር፣ ዐቅምን በመገንባት እና የውይይት መድረኮችን በማመቻቸት ረገድ ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።