የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተመረጡ የደቡብ ኦሞ ዞን የአርብቶ አደር አካባቢዎች የትምህርት መብት አተገባበርን አስመልክቶ ባከናወነው የሰብአዊ መብቶች ክትትል በተለዩ ግኝቶች እና በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ላይ ሰኔ 23 ቀን 2018 ዓ.ም. በጂንካ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አካሂዷል። በውይይቱ ከደቡብ ኦሞ ዞን ትምህርት መምሪያ፣ ከመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት መምሪያ፣ ከቱርሚ ከተማ አስተዳደር፣ እንዲሁም ከኛንጋቶም፣ ከማሌ እና ከበና ጸማይ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤቶች እና ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።


በመድረኩ ኢሰመኮ የትምህርት መብት በዓለም አቀፍ እና በሀገራዊ የሕግ ማዕቀፎች የተሰጠውን ጥበቃ ጨምሮ፣ በአርብቶ አደር አካባቢዎች የመብቱ አተገባበር ላይ ባከናወነው ክትትል የተለዩ ግኝቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል። በአከባቢው የትምህርት መብትን አተገባበር ለማሻሻል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች እንዳሉ ሆነው በርካታ ትምህርት ቤቶች በጎርፍ እና በከፍተኛ ንፋስ ምክንያት ጉዳት የሚደርስባቸው መሆኑ፤ በተለይም በዳሰነች ወረዳ ከ20 በላይ ትምህርት ቤቶች በውኃ መዋጣቸው፣ ከፍተኛ የመምህራን መለዋወጥና ፍልሰት መኖሩ፣ በትምህርት ገበታ የሴት ተማሪዎች ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆን እንዲሁም ለትምህርት ዘርፉ የሚመደበው ልዩ የበጀት ድጋፍ (Block Grant) ካለው የገበያ ዋጋ አንጻር በቂ አለመሆኑ በውይይቱ በተግዳሮትነት ተነስተዋል።


የውይይቱ ተሳታፊዎች ስለ ትምህርት አስፈላጊነት ግንዛቤ መፍጠርና የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ፣ ለመምህራን የስልጠና እድሎችን ማመቻቸት፣ ተንቀሳቃሽ ትምህርት ቤቶችን እና ሆስቴሎችን (አዳሪ ትምህርት ቤቶችን) ማስፋፋትና ማጠናከር እንዲሁም ለትምህርት ቤቶች አስፈላጊውን በጀት በመመደብ ግብዓት ማሟላት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢሰመኮ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሥራ ክፍል ኃላፊ ሃዊ አስፋው፤ በአርብቶ አደር አካባቢዎች የሚስተዋለውን የትምህርት መብት አተገባበር ክፍተት ለመቅረፍ የአካባቢዎቹን ሁኔታ ያገናዘበ ምላሽ እና የባለድርሻ አካላትን የተቀናጀ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም የትምህርት መብትን ለማረጋገጥ መሠረታዊ መስፈርቶች የሆኑትን ተደራሽነትን፣ ተገኝነትን፣ ተቀባይነትን እና ተስማሚነትን ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።