በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት ሲካሄድ የነበረው 6ኛው ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ምስለ-ችሎት (6th National High Schools Human Rights Moot Court Competition) ውድድር ሚያዝያ 16 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በተካሄደ የፍጻሜ ውድድር ተጠናቋል፡፡ ውድድሩ ከጥር 23 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በክልሎች እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን በ12 ክልሎች እና 2 ከተማ አስተዳደሮች ከሚገኙ 91 ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 182 ተወዳዳሪ ተማሪዎች ተሳትፈውበታል።

በክልሎች እና በከተማ አስተዳደር ደረጃ በተካሄደው የምስለ ችሎት ውድድር ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገቡ 8 ቡድኖች ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመምጣት የሩብ እና የግማሽ ፍጻሜ ሀገር አቀፍ የቃል ክርክር ውድድር ከሚያዝያ 12 እስከ 16 ቀን 2018 ዓ.ም. ሲያደርጉ ቆይተው የፍጻሜ ውድድር አድርገዋል፡፡

በፍጻሜ ውድድሩ ተማሪ መርስን ተፈራ እና ተማሪ ቦንቱ ታደሰ ከአዲስ አበባ ከተማ እቴጌ መነን የሴቶች አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም ተማሪ ይዲድያ ብሩክ እና አናቤል ነብዩ ከደብረብርሃን ከተማ ሀይሌ ማናስ አካዳሚ አመልካችና ተጠሪን ወክለው የቃል ክርክራቸውን አካሂደዋል። በዚሁ መሠረት:-

ተማሪ መርሰን ተፈራ እና ቦንቱ ታደሰ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እቴጌ መነን የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት የፍጻሜ ውድድሩ አሸናፊዎች ሆነዋል፡፡

ተማሪ አናቤል ነብዩ ከደብረብርሃን ከተማ ሀይሌ ማናስ አካዳሚ የውድድሩ ምርጥ የቃል ተከራካሪ በመሆን ያሸነፈች ሲሆን፤

ተማሪ ኪብሮን ነጻነት እና ተማሪ ዲኒያ ናስር ከሸገር ከተማ ሒል ቶፕስ አካዳሚ በምርጥ የጽሑፍ ክርክር አሸናፊዎች ሆነዋል፡፡

የዘንድሮው ውድድር ምናባዊ ጉዳይ ትኩረቱን ያደረገው የመማር መብት በግጭት ዐውድ ውስጥ” (The Right   to Education in the Context of Armed Conflict) ላይ ሲሆን፣ የትምህርት መብትን በተለይም የትምህርት ተገኝነትን (availability) ተደራሽነትን (accessibility)፣ ተቀባይነትን (acceptability) እና ተላማጅነትን (adaptability)፤ በግጭት ዐወድ ውስጥ የትምህርት መብት መርሖችን እንዲሁም የትምህርት መብትን ከማክበር፣ ማስከበር እና ማሟላት አኳያ የመንግሥት መሠረታዊ ግዴታዎችን የተመለከቱ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መመዘኛዎች ላይ ተመሥርቷል።  ይህም በግጭት ዐውድ ውስጥ የትምህርት ቀጣይነትን የተመለከቱ የሰብአዊ መብቶች መመዘኛዎችን በማንሳት ተወዳዳሪ ተማሪዎች በመብቶቹ ዙሪያ ጥልቅ ውይይትና ንባብ እንዲያደርጉ እና ዕውቀት እንዲያካብቱ አጋጣሚ ፈጥሯል።

የምስለ ችሎት ውድድሩ በሕግና ሰብአዊ መብቶች ባለሙያዎች የተዳኘ እና የመደበኛ ፍርድ ቤት ክርክር ሥርዓትን የተከተለ ሲሆን፤ ተወዳዳሪ ተማሪዎች ተገቢው ገለጻና አጭር ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ ለውድድሩ በተመረጠው ምናባዊ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ (hypothetical case) ላይ አመልካች እና ተጠሪን በመወከል የጽሑፍ እና የቃል ክርክር ያደረጉበትም ነው።

በዚህ የፍጻሜ ውድድር ላይ የኢሰመኮ ኮሚሽነሮችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የክልል ትምህርት ቢሮዎች ተወካዮች፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የተወዳዳሪ ተማሪዎች ቤተሰቦች እንዲሁም ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ሚዛኔ አባተ ኢሰመኮ የወጣቶችን የሰብአዊ መብቶች ግንዛቤና ክህሎት ለማሰደግ እንዲሁም አመለካከት ለመቀየር ከሚጠቀምባቸው ስልቶች መካከል የምስለ ችሎት ውድድር አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ በግጭት ዐውድ ውስጥ የትምህርት ቀጣይነትን ማረጋገጥ ሀገር ተረካቢ ትውልድ በመፍጠር ሀገራት ከግጭት ዐውድ ውስጥና ከሰብአዊ መብቶች ጥሰተቶች አዙሪት ሊወጡ የሚችሉበት የተሻለ አማራጭ መሆኑን ተረድተው፣ ይህንኑ በውድድሩ የተለያዩ ዙሮች ላይ ለተሳተፉ ተማሪዎች፣ የትምህርት ቤት ማኅበረሰብ አባላት፣ ወላጆች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ማስገንዘብ እንደቻሉ ገልጸዋል። አክለውም “6ኛው ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የሰብአዊ መብቶች ምስለ ችሎት ውድድር ወቅታዊ እና ሀገራዊ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳዎችን ተገንዘቦ አስተዋጽዖ የማድረግ ዐቅም ያለው ትውልድ በማፍራት ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን እውን ማድረግ እንድንችል ዕድል የሠጠን ነው” ብለዋል።