የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በባሕር ዳር፣ በጅግጅጋ እና በሃዋሳ ከተሞች ያካሄደውን ግልጽ የምርመራ መድረክ ተከትሎ በአዳማ ከተማ ከሚያዝያ 17 እስከ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ አራተኛውን ግልጽ የምርመራ መድረክ በማካሄድ በተለይ የዘፈቀደ እስርን፣ የተራዘመ የቅድመ ክስ እስር እና በእስር ወቅት ተከስተዋል ስለተባሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጎጂዎች እና ምስክሮች ያቀረቧቸውን አቤቱታዎች እንዲሁም ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት የተሰጡ ምላሾችን አዳምጧል።
ለአብነት ተመርጠው ከቀረቡት 18 አቤቱታዎች መካከል ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝ እና መደበኛ ባልሆኑና በማይታወቁ ቦታዎች በእስር ማቆየት፣ በሕግ በተቀመጠው ጊዜ መሠረት የታሰረን ሰው ፍርድ ቤት ያለማቅረብ፣ የፍርድ ቤት የዋስትና መብት ትእዛዝ አለማክበር ይገኙበታል። በተጨማሪም የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብትን፣ በእስር ወቅት በቤተሰብ የመጎብኘት መብትን፣ በቂ ምግብ፣ ውሃ፣ መጸዳጃ እና ሕክምና የማግኘት መብትን አለማክበር እና ጭካኔ የተሞላበትና የማሰቃየት ድርጊት መፈጸም በቀረቡት አቤቱታዎች በተደጋጋሚ ከተጠቀሱት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መካከል ናቸው፡፡
የግልጽ ምርመራ መድረክ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ደርሶብናል የሚሉ ሰዎች፣ ምስክሮች፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግሥት ተወካዮች በአንድ መድረክ በተገኙበት በሕዝብ ፊት የሚከናወን የምርመራ ስልት ነው። አቤቱታ አቅራቢዎች ደርሶብናል የሚሏቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በግልጽ መድረክ ምስክርነት መስጠትና ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ ሲሆን የሚሰጡት ቃል ሚስጥራዊ ባሕርይ ወይም የደኅንነት ሥጋት ያለባቸው ሰዎች ደግሞ በልዩ ሁኔታ በሚስጥር ቃላቸውን የሚሰጡበትን ዕድልንም ያካትታል፡፡
ለግልጽ ምርመራው በኦሮሚያ ክልል ነጻነታቸውን ከሕግ አግባብ ውጪ እና በዘፈቀደ የተነፈጉ ሰዎች መብቶች ላይ ያተኮረ ጥናትና ምርምር ወይም የምርመራና ክትትል ግኝቶች ያሏቸው አካላት ይህንኑ እንዲያቀርቡ ኮሚሽኑ ያደረገውን ጥሪ ተከትሎ መቀመጫውን በውጭ ሀገር ያደረገ Oromo Legacy Leadership & Advocacy Association/OLLAA የተባለ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅትን ጨምሮ ሌሎችም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የየበኩላቸውን መረጃዎችና ትንተናዎች በጽሑፍ ለኮሚሽኑ ያስገቡ ሲሆን፣ በግልጽ ምርመራ መድረኩም ላይ በበይነ መረብ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ዋና ዋና ሐሳቦቻቸውን አቅርበዋል፡፡ ሌሎች የሲቪል ማኅበራት ተወካዮችም ከሕግ ውጪ የሆኑና የዘፈቀደ እስራትን በተመለከተ አጣርተን ደርሰንበታል ያሉትን መረጃዎች በመድረኩ አቅርበው የመንግሥት አካላት ምክረ ሐሳቦቻቸውን በመቀበል ተግባር ላይ እንዲያውሉና ለሰብአዊ መብቶች መከበር አብረዋቸው እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተጨማሪም አባ ገዳዎችና ሀዳ ስንቄ ተወካዮች እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችም በበኩላቸው ያስተዋሏቸውን ችግሮች አስረድተው ለክልሉ ሰላምና የሰብአዊ መብቶች መከበር የየራሳቸውን ድርሻ እየተወጡ እንዳለና ይህንንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል እና በተለያዩ ዞኖች በየደረጃው ያሉ የፍርድ ቤት፣ የፍትሕ ቢሮ፣ የፖሊስ ኮሚሽን እና የሰላምና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ተወካዮች ለቀረቡት አቤቱታዎችና ተፈጽመዋል ስለተባሉት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፤ በተጨማሪም የፍትሕ እና የጸጥታ ተቋማቱ ያሉባቸውን ተግዳሮቶች እንዲሁም ለመብት ጥሰቶቹ መነሻ ምክንያት የሆኑ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታም አስረድተዋል:: በአዳማ ከተማ የተካሄደውን ግልጽ ምርመራ መድረክ የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል፣ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ እና የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ኢማድ አብዱልፈታህ መርተውታል፡፡ የዝግጅቱን መጠናቀቅ ተከትሎ የመርማሪ ኮሚሽነሮች ሰብሳቢ ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል “በግልጽ የምርመራ መድረኩ ተጎጂዎች፣ ባለግዴታዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ዙሪያ በግልጽ መነጋገር መቻሉ እንዲሁም ለወደፊት ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች በሁሉም አካላት በኩል ለመደጋገፍ የመፍትሔ ሐሳቦች መቅረባቸው የሚያበረታታ ነው” ብለዋል።