የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከዴንማርክ የሰብአዊ መብቶች ተቋም (Danish Institute for Human Rights (DIHR)) እና ከኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር በመተባበር ንግድ እና ሰብአዊ መብቶች ላይ ያተኮረ የዐቅም ግንባታ ስልጠና ሐምሌ 18 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል። መድረኩ በንግድ ዐውድ ውስጥ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመለየት፣ ለመከላከል እና ለመቀነስ የሚያስችሉ የጥንቃቄ ሂደቶችን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) የንግድ እና ሰብአዊ መብቶች መመሪያ መርሖችን (United Nations Guiding Principles on Business and Human Rights) እንዲሁም በዝግጅት ሂደት ላይ የሚገኘውን የንግድ እና የሰብአዊ መብቶች ብሔራዊ የድርጊት መርኃ ግብር በተመለከተ የንግዱን ማኅበረሰብ ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ ነው።






በስልጠናው አስመጪ እና ላኪዎች፣ አገልግሎት ሰጪዎች፣ አምራቾችን ጨምሮ በተለያዩ የንግድ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ድርጀቶች እንዲሁም የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የዴንማርክ የሰብአዊ መብቶች ተቋም እና የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በስልጠናው የተባበሩት መንግሥታት የንግድ እና ሰብአዊ መብቶች መመሪያ መርሖች መሠረታዊ ይዘቶችን አስመልክቶ በተለይም የንግድ ተቋማት ሰብአዊ መብቶችን የማክበር ኃላፊነትን በተመለከተ በዴንማርክ የሰብአዊ መብቶች ተቋም የምሥራቅ አፍሪካ ተወካይ ዶ/ር ኦጆት ሚሩ ገለጻ ተደርጓል። በመቀጠልም በኢትዮጵያ ያለው የንግድ እና ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ፣ ኢሰመኮ በንግድ ዐውድ ውስጥ የሰብአዊ መብቶችን መከበር ለማረጋገጥ የሚያደርጋቸው ጥረቶች፣ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት መመሪያ መርሖችን በመተግበር የሚገኘው ጥቅም፣ የንግድ እና ሰብአዊ መብቶች ብሔራዊ የድርጊት መርኃ ግብር ምንነትና አስፈላጊነት እንዲሁም በዝግጀት ሂደቱ ታሳቢ ሊደረጉ የሚገቡ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

በፍትሕ ሚኒስቴር መሪነት እየተከናወነ ያለው የንግድ እና ሰብአዊ መብቶች ብሔራዊ የድርጊት መርኃ ግብር ዝግጅት የደረሰበትን ደረጃ፣ የንግዱ ማኅበረሰብ ተሳትፎ እና በቀጣይም ከንግዱ ማኅበረሰቡ ጋር የሚካሄዱ ውይይቶችን አስመልክቶ በፍትሕ ሚኒስቴር የሰብአዊ መብቶች ዳይሬክተር አወል ሱልጣን ገለጻ አድርገዋል።


የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የቢዝነስ አመራር አካዳሚ ዳይሬክተር ብስራት በለጠ የንግድ ተቋማት በዓለም አቀፍ ደረጃ በተቀመጡ መስፈርቶችመሠረት ሰብአዊ መብቶችን በማክበር መሥራታቸው የገበያ ትስስርን ከማጠናከር፣ መልካም ስምን ከመገንባት እና ከመጠበቅ አንጻር ከፍተኛ ጥቅም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል የንግድ ድርጅቶች ለሰብአዊ መብቶች መከበር ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ሆኖም ግን ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች አስተዋጽዖ እንዳያደርጉ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል።