የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለ6ኛ ጊዜ ለሚያካሄደው ሀገር አቀፍ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ምስለ-ችሎት (Moot Court) ውድድር ከክልል እና ከከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አስተባባሪዎች ጋር ታኅሣሥ 21 ቀን 2018 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ የማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓትና ውይይት አካሂዷል፡፡ በመርኃ ግብሩ ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የምስለ-ችሎት ውድድር አስተባባሪዎች እንዲሁም የሥርዓተ-ትምህርት ዳይሬክተሮች ተሳትፈዋል።



በኢሰመኮ አዘጋጅነት በየዓመቱ የሚካሄደው ይህ ውድድር ታዳጊ ተማሪዎች በሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ዕውቀት፣ አመለካከት እና ክህሎት ለማሳደግ ያለመ ሲሆን፣ ተማሪዎች ለውድድር በተመረጠ አንድ ምናባዊ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ (hypothetical case) ላይ በመመሥረት የአመልካች እና የተጠሪ ወገኖችን በመወከል የጽሑፍ እና የቃል ክርክር የሚያደርጉበት ነው፡፡ የምስለ ችሎት ውድድሩ በሕግና ሰብአዊ መብቶች ባለሙያዎች የሚዳኝ፣ ከሞላ ጎደል የመደበኛ ፍርድ ቤት ክርክር ሥርዓትን የሚከተል አስተማሪ የውድድር ዐይነት ነው።



በመርኃ ግብሩ በ2017 ዓ.ም. የተካሄደው 5ኛው የሰብአዊ መብቶች ምስለ ችሎት ውድድር ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ በውድድሩ መመሪያዎች ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች ለውይይት ቀርበው ጸድቀዋል፡፡ በተጨማሪም 6ኛው ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ምስለ ችሎት ውድድር የሚከናወንበት የጊዜ ሰሌዳ እና ዝርዝር ተግባራት ላይ ውይይት ተደርጎ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ በውድድሩ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባም ተገልጿል።



የውይይቱ ተሳታፊዎች የምስለ ችሎት ውድድር የሰብአዊ መብቶች ባህልን በተማሪዎች እና በትምህርት ማኅበረሰቡ ዘንድ ለማጎልበት እንዲሁም ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ያገኙትን ዕውቀት በተግባር ለማዳበር ዐይነተኛ ስልት መሆኑን ጠቅሰው፣ መሰል ውድድሮችን እና የሰብአዊ መብቶች ክበባትን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር መቅደስ ታደለ የሰብአዊ መብቶች የምስለ ችሎት ውድድር ኢሰመኮ ትኩረት ሰጥቶ ከሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑን በመግለጽ ውድድሩ ውጤታማ እና የተሳካ እንዲሆን የክልል እና ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አስተባባሪዎች እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። ውድድሩ በየዓመቱ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ሲካሄድ የቆየ መሆኑን በማስታወስ፣ የዚህ ዓመት ውድድር “የመማር መብት በትጥቅ ግጭት ዐውድ ውስጥ” (“The Right to Education in Situation of Armed Conflict”) የሚል ርእስ በተሰጠው ምናባዊ ጉዳይ ላይ እንደሚያተኩር ይፋ አድርገዋል።