የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኢሰመኮ ባለፈው ስድስት ወር በተከናወኑ ተግባራት የተገኙ ውጤቶች፣ አበረታች እርምጃዎች እና ተግዳሮቶችን በተመለከተ የካቲት 17 ቀን 2018 ዓ.ም. በኢሰመኮ ዋና መሥሪያ ቤት ጋዜጣዊ ጉባኤ አካሂዷል። በጋዜጣዊ ጉባኤው መገናኛ ብዙኀን እና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

ጋዜጣዊ ጉባኤው ሀገራችን ኢትዮጵያ የአፍሪካ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ትስስርን (Network for African National Human Rights Institutions (NANHRI)) ጠቅላላ ጉባኤ እና 16ኛ ኮንፈረንስ በ2019 ዓ.ም. (እ.አ.አ. በ2027) እንድታዘጋጅ መመረጧን እና የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ የትስስሩ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው መመረጣቸውን ይፋ ለማድረግ እና ተቋማዊ፣ ሀገራዊና አህጉራዊ ፋይዳውን ለማስገንዘብ እንዲሁም በ2018 ዓ.ም. የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት በተከናወኑ የሰብአዊ መብቶች ክትትል፣ ምርመራ እና ውትወታ ሥራዎች የተስተዋሉ ዐበይት አበረታች እርምጃዎችን እና ተግዳሮቶችን ይፋ ለማድረግ ያለመ ነው።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት ትስስር (NANHRI) ጠቅላላ ጉባኤን እና 16ኛውን ኮንፍረንስ እንድታስተናግድ እና የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ የትስስሩ ም/ሰብሳቢ ሆነው ስለመመረጣቸው 

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በጋዜጣዊ ጉባኤው ላይ በሰጡት መግለጫ የአፍሪካ ብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት ትስስር (NANHRI) ጥር 27 ቀን 2018 ዓ.ም. (February 4, 2026) በካሜሮን/ያውንዴ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ (General Assembly) ኢትዮጵያ ቀጣዩን ጠቅላላ ጉባኤ እና 16ኛውን ኮንፍረንስ እንድታዘጋጅ በጠቅላላ ጉባኤው በሙሉ ድምጽ መመረጧን ይፋ አድርገዋል። ይህንንም ተከትሎ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ለቀጣይ ሁለት ዓመታት የትስስሩ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው በተመሳሳይ ድምጽ መመረጣቸው ተገልጿል።

የአፍሪካ ብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት ትስስር (NANHRI) 47 የአፍሪካ ሀገራት ብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት በአባልነት ያቀፈ እና ጽሕፈት ቤቱን ናይሮቢ አድርጎ በ እ.አ.አ. 2007 የተቋቋመ ቀጠናዊ ድርጅት ሲሆን በአፍሪካ ነፃ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት እንዲመሠረቱ፣ በትብብር እንዲሠሩ እና በአጠቃላይ በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት ሰብአዊ መብቶችን እንዲያስከብሩ እና እንዲያስፋፉ ይደግፋል። ትስስሩ በመመሥረቻው ሕግ አንቀጽ 28 እና 56 መሠረት በየሁለት ዓመቱ አጠቃላይ ጉባኤውን እንዲሁም ትኩረቱን በአፍሪካ ሰብአዊ መብቶች አተገባበር ሁኔታ ላይ ያደረገ እና የአፍሪካ ቀጠናዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም የትምህርትና የምርምር ተቋማት የሚሳተፉበት ኮንፍረንስ ያካሂዳል።

ሀገራችን ጉባኤዎቹን ለማስተናገድ ያሳየችው ቁርጠኝነትና የመንግሥት ድጋፍ፣ ኢሰመኮ ከዓለም አቀፍ፣ ከአህጉራዊ እና ከአጋር አካላት ጋር ትብብርን በማጠናከር ያደረገው ንቁ ትብብር እና ተሳትፎ እንዲሁም ኢሰመኮ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ለሰብአዊ መብቶች መከበርና መስፋፋት እያደረገ ያለው አስተዋጽዖ የትስስሩን ጠቅላላ ጉባኤ እና ዓመታዊ ኮንፍረንስ ለማዘጋጀት እንድትመረጥ ያስቻሉ መስፈርቶች መሆናቸው በጋዜጣዊ መግለጫው ተመላክቷል።

የትስስሩ ጠቅላላ ጉባኤ እና ኮንፍረንስ በሀገራችን ኢትዮጵያ መዘጋጀቱ ኢሰመኮ ለሰብአዊ መብቶች መጠበቅና ማስፋፋት እያደረገ ላለው አስተዋጽዖ ዕውቅና የሚሰጥ፤ እንደ ሀገር አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተደማጭነታችን እንዲጨምር የሚያደርግ እና ኢሰመኮ ወደፊት አጠናክሮ ለሚሠራቸው ሥራዎች ከሌሎች አቻ ተቋማት ልምድ ለመቅሰም የሚያስችል ሚና እንደሚኖረው ተጠቁሟል። በተጨማሪም መንግሥታዊ ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የትምህርትና ምርምር ተቋማት እንዲሁም ፖሊሲ አውጪዎች ከተለያዩ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማትና መሪዎች፣ ከተመራማሪዎች፣ ከብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት ተወካዮች ጋር እንዲገናኙ፣ እንዲመክሩ እና እንዲተሳሰሩ መድረክ በመፍጠር አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው ዋና ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።

ከዚህም ጋር በተያያዘ ኢሰመኮ የትስስሩ ንግድ እና ሰብአዊ መብቶች ሥራ ቡድን (NANHRI’s Business and Human Rights Working Group) ምክትል ሰብሳቢ ሆኖ የተመረጠ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ፣ ኢሰመኮ የአፍሪካ ብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት ትስስር ጠቅላላ ጉባኤንና 16ኛው ኮንፍረንስን ለማስተናገድ እንዲችል መንግሥት ላሳየው ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል። በተመሳሳይ ጉባኤዎቹ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄዱ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ቀና ትብብር እና እገዛ እንዲያደርጉ ልባዊ ግብዣ አቅርበው በኢሰመኮ ራሱን የቻለ ሰክሬታሪያት ተቋቁሞ የዝግጅት ሥራዎች ከወዲሁ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በሰብአዊ መብቶች ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት ስለተገኙ አበረታች እርምጃዎች እና ተግዳሮቶች 

ዋና ኮሚሽነር በሰብአዊ መብቶች ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት ስለተገኙ አበረታች እርምጃዎች እና ተግዳሮቶች በሰጡት መግለጫ ባለፈው አንድ ዓመት ከሐረሪ ክልል እና ከድሬ ዳዋ ከተማ አስተዳደር በስተቀር በሁሉም ክልሎች ጉብኝት በማድረግ ከየክልሎቹ ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ አፈ ጉባዔዎች እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች በተገኙበት ሰብአዊ መብቶችን የተመለከቱ ውይይቶች ማድረጋቸውን እና ውይይቶቹን ተከትሎም ክልሎቹ በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ አበረታች እርምጃዎች እየወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም የሰብአዊ መብቶች ምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም ጨምሯል።

ኢሰመኮ በሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች ባለፉት 6 ወራት በአማራ ክልል 186፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 46፣ በጋምቤላ ክልል 66፣ በኦሮሚያ ክልል 915 እንዲሁም በሶማሊ ክልል 123 በአጠቃላይ 1336 ከሕግ አግባብ ውጪ የታሰሩ ሰዎች በነጻ ተፈትተዋል። 122 ሰዎች በዋስትና የተለቀቁ ሲሆን 119 ሰዎች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንዲታይ ማድረግ ተችሏል። በመደበኛ አቤቱታ መቀበያ ሥርዓት 761 አቤቱታዎችን በመቀበል ለ477 ጉዳዮች እልባት ተሰጥቷል። በተንቀሳቃሽ አቤቱታ መቀበያ ስልት ከቀረቡ አቤቱታዎች መካከል 70 አቤቱታዎች መፍትሔ አግኝተዋል። 321 ፖሊስ ጣቢያዎች፣ 42 ማረሚያ ቤቶች እና 9 መደበኛ ያልሆኑ ተጠርጣሪ ማቆያዎች ተጎብኝተዋል። በአብዛኞቹ ማረሚያ ተቋማት ለታራሚዎችና በሕግ ጥበቃ ሥር ላሉ ሰዎች የቀን ፍጆታ በጀት መሻሻሉ ከተገኙ አበረታች ውጤቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ከሲቪልና ከፖለቲካ መብቶች ጋር በተያያዘም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በመልክዓ ምድራዊ የመረጃ ሥርዓት (Geographical Information System (GIS)) በመታገዝ የምርጫ ጣቢያዎችን የመለየት፣ የጽሕፈት ቤቶቹን ብዛት ወደ 22 ከፍ በማድረግ ተደራሽነቱን ማስፋቱ፣ እንዲሁም መራጮችና ዕጩዎች ባሉበት ቦታ ሆነው መመዝገብ የሚችሉበት የዲጂታል ምዝገባ ሥርዓት ማዘጋጀቱ በመልካም እመርታነት ተገልጸዋል። ከምርጫ ጋር በተያያዘ የኢሰመኮ ድርሻ በቅድመ ምርጫ እና በምርጫ ወቅት ሂደቱ ሰብአዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ መካሄዱን መከታተል፣ ሰነዶችን መሰነድ እና ሪፖርት ይፋ ማድረግ መሆኑን በመግለጽ 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫን በዚህ ረገድ ለመከታተልም ኢሰመኮ ቅድመ ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን አብራርተዋል።

በረቂቅ ሂደት ላይ የነበረው የአካል ጉዳተኞች ፖሊሲ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡ እና አህጉራዊው የአካል ጉዳተኞች መብቶች ፕሮቶኮል እንዲጸድቅ ለውጪ ጉዳይ እና ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት መቅረቡ፤ በቅርቡ የጸደቀው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያንን አካቶ ዲዛይን (Inclusive by Design) የስትራቴጂው መርሕ ተድርጎ መካተቱ፤ የአጠቃላይ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 1368/2017 ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የቆየውን ትምህርት የማግኘት መብትን ማካተቱ፣ እንዲሁም ከጤና መብት ጋር በተያያዘ የጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1362/2017 እና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት እና የመድኃኒት ፈንድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1354/2017 ፍትሐዊና ተደራሽ የሆነ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት መዘርጋትን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸው ባለፈው አንድ ዓመት በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ዘርፍ ከታዩ መልካም ውጤቶች መካከል ናቸው።

በሌላ በኩል የመቀነስ ሁኔታ የሚታይበት ቢሆንም በትጥቅ ግጭት ምክንያት በሰው ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት መቀጠሉ፤ በመንገድ ላይ በታጣቂዎች የሚፈጸም እገታ፣ የወንጀል ተጠያቂነት በማያስከትሉ እና የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወይም ውሳኔ በሌለባቸው ጉዳዮች ላይ ከሕግ አግባብ ውጪ እስር (arbitrary arrest) መፈጸሙ፤ በመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ የሚቀርቡ የክስ አቤቱታዎችን ተቀብሎ የወንጀል ምርመራ ለማከናወን አለመቻል በተግዳሮትነት ተዘርዝረዋል።

በተጨማሪም ለታራሚዎች የሚቀርብ የምግብ፣ የጤና እና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ምንም እንኳን መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም በቂ አለመሆን እና በሕግ ጥበቃ ሥር ላሉ ተጠርጣሪዎች በመንግሥት የሚቀርብ የምግብ እና የጤና አገልግሎት በጀት አለመኖር፣ ያለውም በቂ አለመሆን፤ በጋዜጠኞች፣ ጦማሪዎች እና የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች ላይ የሚደርሱ ጫናዎች መኖራቸው፣ በተመሳሳይ በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ዙሪያ አሳሳቢ ተብለው ከተነሱ ጉዳዮች መካከል በማዕድን ዘርፍ የሚታየው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በተለይም በጋምቤላ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በዋናነት ተጠቅሷል።

ኢሰመኮ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ዘርፍ ጋር በተያያዘ የተስተዋሉ ተግዳሮቶች በጋዜጣዊ መግለጫው የተዳሰሱ ሲሆን ከባቢያዊ እና የሕንፃ ተደራሽነት ተግዳሮቶችን ለማስወገድ ቁልፍ ሚና ካላቸው የሕግ ማዕቀፎች መካከል በ2017 በጀት ዓመት የወጣውን የኢትዮጵያ ሕንፃ አዋጅ 1356/2017 ተከትለው እንዲወጡ የሚጠበቁ የአዋጁ ማስፈጸሚያ ደንቦች አለመውጣታቸው፣ የግል እና የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሕንፃዎች ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ እንዲሆኑ የሚያስችል ዝርዝር መስፈርት እንዳይወጣ እንዲሁም የቁጥጥር እና ክትትል ማዕቀፍ እንዳይዘረጋ ክፍተት መፍጠሩ ተመላክቷል።

ከዚህም ባሻገር በአብዛኛዎቹ የምክረ ሐሳብ አፈጻጸም ክትትሎች በተደረጉባቸው እርሻ ጣቢያዎች አበረታች እርምጃዎች ቢኖሩም አሁንም ለሴት እና ወጣት ሠራተኞች የአደጋ እና የበሽታ መከላከያ አልባሳት፣ ቁሳቁሶች እና ሌሎች ግብአቶች ሙሉ ለሙሉ ወይም በበቂ ሁኔታ አለመቅረባቸው፣ ለጊዜያዊ ሠራተኞች የቅድመ እና የድኅረ ወሊድ ፈቃድ ከክፍያ ጋር አለመሰጠቱ፤ የሳምንት እና የበዓል ቀናት እረፍት በሕጉ መሠረት ለሠራተኞች የሚሰጥ አለመሆኑ፣ ተመሳሳይ ሥራ ለሚሠሩ ቋሚ እና ጊዜያዊ ሠራተኞች ተመሳሳይ ክፍያ እንዲሁም የትርፍ ሰዓት ሥራ ክፍያ በሕጉ መሠረት ተሰልቶ የማይከፈል መሆኑ፤ ለሴት እና ወጣት ሠራተኞች የተከለከሉ ሥራዎችን ወጣት ሴቶች እንዲሠሩ መደረጉ፤ የሠራተኞች ደመወዝ ወቅቱን ጠብቆ እየተከፈለ አለመሆን ቀጣይነት ያለው የምክረ ሐሳብ አፈጻጸም ክትትል እና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጡ እርምጃዎች እንዲወሰዱ የሚያመላክቱ መሆናቸውን ዋና ኮሚሽነር በመግለጫቸው አንስተዋል።

የኢሰመኮ ተቋማዊ ሥራዎች እና የተመዘገቡ ቁልፍ ውጤቶችን በሚመለከት 

በጋዜጣዊ ጉባኤው የኢሰመኮ ተቋማዊ ሥራዎች እና የተመዘገቡ ቁልፍ ውጤቶች የተዳሰሱ ሲሆን በፓሪስ መርሖች መሠረት የኢሰመኮን አመራሮች እና ሠራተኞች ቅጥር እና ምደባ የሃይማኖት፣ የጾታ፣ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የአካል ጉዳተኝነት ብዝኅነትን ባማከለ አግባብ መፈጸም የሚያስችል የብዝኅነት መመሪያ ጸድቆ እየተተገበረ መሆኑ፣ አካላዊ ተደራሽነቱን ለማስፋት 5 ተጨማሪ የከተማ ጽሕፈት ቤቶች መከፈታቸው፣ አማርኛ እና እንግሊዝኛን ጨምሮ በአፋን ኦሮሞ፣ በትግርኛ እና በሶማሊኛ ቋንቋ በመጠቀም የሰብአዊ መብቶች መረጃ ተደራሽነትን ለማጎልበት ወደ ተግባር የተገባ መሆኑ ጠቁሟል። 

በተመሳሳይ ከመንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር የተጀመሩ የትብብር እና የአጋርነት ግንኙነቶች ተጠናክረው መቀጠላቸው ተነግሯል። በዚህም የሰብአዊ መብቶች ምክረ ሐሳቦችን ከሞላ ጎደል ማስፈጸም መቻሉን፣ የመብቶች ጥሰቶች ከመፈጸማቸው በፊት መከላከል የሚያስችል ዝግጁነት እና በባለድርሻ አካላት ዘንድ ቀና አመለካከት መፈጠሩ እንዲሁም በሀገራችን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን ለማሻሻል የሚያግዙ ፕሮጀክቶች መቀረጻቸው እና ተገቢው የፋይናንስ ድጋፍም መገኘቱን ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ዋና ኮሚሽነር በጋዜጣዊ ጉባኤው የተሳተፉ የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች በአሁናዊ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ ላነሷቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል። ከዘፈቀድ እስር እና አስገድዶ መሰወር ጋር በተገናኘ ለተነሱ ጥያቄዎች ኢሰመኮ የቀረበለትን አቤቱታ ተከትሎ ክትትል እንደሚያደርግ እና የማጣራት ሥራ እንደሚሠራ፤ ኢሰመኮ መንግሥትን ጨምሮ የማንኛውም አካል ጫና እንደሌለበት፤ የነጻነትና የገለልተኝነት መርሕን መሠረት አድርጎ ከመንግሥትና ከዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ጋር እንዲሁም ሌሎች ለሰብአዊ መብቶች መከበር ያግዛሉ ካላቸው ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሠራ፤ ከማንኛውም ተጽዕኖ ነፃ መሆኑ በሥራዎቹና በሚያቀርባቸው ሪፖርቶች መረዳት እንደሚቻል፤ ሰብአዊ መብቶችን ያከበረ እና ማዕከል ያደረገ የሽግግር ፍትሕ እንዲተገበር ኢሰመኮ የሚጠበቅበትን እየተወጣ መሆኑን ዋና ኮሚሽነር በዝርዝር አብራርተዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በማጠቃለያ መልእክታቸው ኢሰመኮ በተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ግኝቶች ላይ የሚሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች በተሟላ ሁኔታ መፈጸማቸው የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታን ማሻሻል እንደሚያስችል ገልጸዋል። በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ የሚሠሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና የሚመለከታቸው ሌሎች ባለድርሻዎች ኢሰመኮ የሚሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች በተሟላ ሁኔታ እንዲተገበሩ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም አሳስበዋል። አክለውም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኢሰመኮ የአፍሪካ ብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት ትስስር ጠቅላላ ጉባኤ እና 16ኛው ኮንፍረንስ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ቀና ትብብር እና እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።