የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ጽሕፈት ቤት (Office the High Commissioner for Human Rights- East Africa Regional Office, (OHCHR-EARO)) ጋር በመተባበር ከጥር 19 እስከ 21 ቀን 2018 ዓ.ም. በሽግግር ፍትሕ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል። በመድረኩ የድሬ ዳዋ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ከአፋር፣ ከአማራ፣ ከቤንሻንጉል-ጉሙዝ፣ ከሐረሪ፣ ከሶማሊ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ፣ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ከትግራይ ክልሎች የተውጣጡ የተጎጂዎች ማኅበራት (Victims’ Associations) ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የውይይት መድረኩ የተጎጂዎች ማኅበራትን በማጎልበት በሽግግር ፍትሕ ሂደት ውጤታማ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የቴክኒክ እና የውትወታ ዐቅማቸውን ለማሳደግ ያለመ ሲሆን ኢሰመኮ እና OHCHR-EARO እ.ኤ.አ. ከ2023 ጀምሮ ያካሄዷቸውን ተደጋጋሚ ውይይቶች መሠረት በማደረግ ተጎጂዎች በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለመርዳት የተዘጋጀ ነው። ከዚህ በፊት የተካሄዱ የአቻ-ለአቻ የመማማር ፕሮግራሞች እንዲሁም በቀጣይነት እየተካሄዱ ያሉ የተደራሽነት እና የማስረጽ ተግባራት የተጎጂዎች ማኅበራትን በማጠናከር፣ ትብብርን በማሳደግ እና በተለያዩ ክልሎች አዳዲስ ማኅበራትን በማቋቋም በኩል ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።

“የማሰቃየት ሰለባዎች ማዕከል” (Center for Victims of Torture (CVT)) ባለሙያዎች፤ የሰብአዊ መብቶች ሥራ በደህንነት ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ፣ ስለ ራስን የመንከባከብ ልምዶች እና ስለ ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት ግንዛቤ ያለው እንክብካቤ (trauma-informed care) እንዲሁም በተጎጂዎች እና ከጥቃት የተረፉ ሰዎች (Victims and Survivors) ላይ የሚደርሰውን ስሜታዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጫና ግምት ውስጥ ያስገባ ውትወታ ዙሪያ ስልጠናዎችን ሰጥተዋል። የውይይት መድረኩ ተጎጂዎች እና ከጥቃት የተረፉ ሰዎች ለመብቶቻቸው በሚሟገቱበት ወቅት የሚጋፈጧቸውን ልዩ አደጋዎች ታሳቢ ያደረገ፣ ስለ መሠረታዊ የደህንነት ሥጋት አመራር፣ ስለ ሥጋት ትንተና እና ስለ ድንገተኛ አደጋ ምላሽ አሰጣጥ ያተኮሩ ስልጠናዎችንም አካትቷል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ትስስር (Ethiopian Civil Societies Network) ተወካይ በትስስር ፈጣራ እና አስተዳደር ላይ ያላቸውን ተሞክሮ አጋርተዋል።


የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የቴክኒክ ድጋፎች ይበልጥ እንዲጠናከሩ፣ በተለይም ለአእምሮ ጤና እና ለሥነ-ልቦና እና ማኅበራዊ ድጋፍ (MHPSS) ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ፣ እንዲሁም በቅንጅት መሥራት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚገባ በተደጋጋሚ ያሳሰቡ ሲሆን በተጎጂዎች ማኅበራት መካከል ቅንጅታዊ አሠራር እና ተቀራርቦ የመሥራት ባህልን ለማሳደግ ያግዛሉ ያሏቸውን ስልቶች/ስትራቴጂዎች አጋርተዋል። ውይይቱ የጋራ የሆኑ ጉዳዮች የተለዩበት እና የተጎጂዎች ድምጽ እንዲሰማ፣ ፍላጎቶቻቸው እንዲሟሉ እንዲሁም በሽግግር ፍትሕ ሂደት ሁለንተናዊ እና የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚያግዝ መሆኑንም ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ቃልኪዳን ደረጄ ኢሰመኮ የተጎጂዎች ማኅበራትን የቴክኒክ፣ የሥነ-ልቦና እና ማኅበራዊ (psychosocial) እንዲሁም የውትወታ ዐቅማቸውን ለማሳደግ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። ዕውቀትን በማካፈል እና ቅንጅታዊ አሠራሮችን በማጎልብት እነዚህ ማኅብራት የተጎጂዎች ድምጽ እንዲሰማ፣ ጥያቄዎቻቸው ምላሽ እንዲያገኙ ብሎም በሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያስችላቸውን ዐቅም ማግኘታቸውን በአጽንዖት ገልጸዋል። አክለውም፣ እነዚህ እንደነዚህ ዓይነት ጥረቶች ተጠያቂነትን ከማሳደግ እና ፍትሕን ከማስፈን ባሻገር ሰፊ ማኅበራዊ ለውጥን የሚያመጡ መሆኑን አመላክተዋል። በመጨረሻም በሽግግር ፍትሕ ሂደቱ የተጎጂዎች ድምጽ እንዲሰማ እና ፍላጎቶቻቸው ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኙ ኢሰመኮ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።