የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለአረጋውያን የሚቀርብ የሴፍቲኔት አገልግሎት ተደራሽነት እና ጥራትን አስመልክቶ ባካሄደው የሰብአዊ መብቶች ክትትል በተለዩ ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የካቲት 19 ቀን 2018 ዓ.ም. የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ አካሂዷል። ክትትሉ በአፋር፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሊ እና በትግራይ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ ከተሞች፣ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች የተካሄደ ነው።
በመድረኩ ከሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ፣ ከከተማ እና መሠረተ ልማት እና ከግብርና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ ክትትሉ ከተከናወነባቸው ክልሎች እና ከተማ አስተዳደር ማኅበራዊ ጉዳይ፣ ከተማ እና መሠረተ ልማት እና ግብርና ቢሮዎች፣ ከአረጋውያን ማኅበራት የተወጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

በመድረኩ ኢሰመኮ በክትትሉ የለያቸው ቁልፍ እመርታዎች፣ አሳሳቢ ጉዳዮች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፤ ባለድርሻ አካላትም የሴፍቲኔት አገልግሎትን ለአረጋውያን በተሻለ ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግና የአረጋውያን ማኅበራዊ ዋስትና የማግኘት መብትን ለማረጋገጥ በተቋሞቻቸው እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን እና የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች አቅርበዋል።

በውይይቱ በአወንታዊነት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል መልማይ ኮሚቴዎች በየደረጃው ካሉ የመንግሥት አካላት እና የማኅበረሰብ አደረጃጀቶች የተውጣጡ መሆኑ፣ በከፊልም ቢሆን የሴፍቲኔት ተጠቃሚ አረጋውያን የጤና መድኅን ተጠቃሚ መደረጋቸው እንዲሁም የአረጋውያን የኢኮኖሚ ሁኔታ ልየታ አሳታፊና የአካባቢውን የኑሮ ሁኔታ እና ዘይቤ ከግምት ያስገባ መሆኑ ተጠቃሽ ናቸው። በሌላ በኩል አረጋውያን የሴፍቲኔት አገልግሎት ምንነትን፣ የአተገባበር ሥርዓቱን እና የቅሬታ አቀራረብ ሂደቶችን አስመልክቶ ያላቸው መረጃ ውስን መሆን፤ በአንዳንድ ቦታዎች ተቆራጭ የሚደረጉ ክፍያዎችን አስመልክቶ ወጥ የሆነ አሠራር አለመከተል፤ በሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች ምልመላ፣ ልየታ እና ትግበራ የአረጋውያን ማኅበራት ተሳትፎ አናሳ መሆን፤ የክፍያዎች መዘግየት፤ የማኅበረሰብ አቀፍ አደረጃጀቶች የቀለም ትምህርት ላልተማሩ በተለይም ለዐይነ ሥውራን እና መስማት ለተሳናቸው አረጋውያን መረጃ ተደራሽ የሚሆንበት አሠራር አለመኖር እንዲሁም የአገልግሎቱ የክትትል እና ቁጥጥር ማዕቀፎች ላይ ውስንነቶች መኖራቸው ተመላክቷል።

የምክክሩ ተሳታፊዎች ከትግበራ ጋር በተገናኘ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን ለመፍታት ራቅ ያሉ እና ገጠራማ አካባቢዎችን በተገቢው መጠን ለመከታተልና ለመደገፍ የሰው ኃይል እና ፋይናንስ አቅርቦትን ማሳደግ፤ በግጭት ምክንያት ክፍያ ተቋርጦባቸው የነበሩ ተጠቃሚዎችን ታሳቢ ያደረገ መፍትሔ መስጠት፤ እንዲሁም ፕሮግራሙ የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን (Community-Based Health Insurance) ሥርዓትን በተሟላ መልኩ እንዲያካትት ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። በምክክር መድረኩ ማጠቃለያ ተሳታፊዎች ከመጡበት ተቋም እና ካላቸው የሥራ ኃላፊነት አንጻር ኢሰመኮ ያስቀመጣቸውን ምክረ ሐሳቦች ለመፈጸም የሚያስችል የድርጊት መርኃ ግብር አዘጋጅተዋል።

የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ጥበቡ ኃይሉ የሴፍቲኔት አገልግሎት የአረጋውያን እና ሌሎች ለኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ዘርፈ ብዙ ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚያስችል ፕሮግራም እንደመሆኑ፤ ተደራሽነቱን እና ጥራቱን በማሳደግ የአረጋውያንን የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚ መብቶች ለማሟላት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል። አክለውም በክትትሉ ለተለዩ ክፍተቶች ምላሽ ለመስጠት እንዲሁም የኢሰመኮ ምክረ ሐሳቦችን ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻዎች በትብብር እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።