የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ የግል እጩዎች እና ጋዜጠኞች በምርጫ ዐውድ ውስጥ በሕግ ሊደረግላቸው ስለሚገባ ጥበቃ አስመልክቶ መጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም.፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል። በመድረኩ ሴት የፖለቲካ ፓርቲ እጩዎች፣ የግል ተወዳዳሪዎች እና ጋዜጠኞች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

በመድረኩ በዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች እና በሀገር አቀፍ የሕግ ማዕቀፎች በምርጫ ወቅት ለሴቶች የተሰጡ ጥበቃዎች እንዲሁም ሴቶች የፖለቲካ ፓርቲ መመስረት/መቀላቀል፣ የምርጫ ቅስቀሳ፣ ሰላማዊ ሰልፍ፣ ስብሰባ፣ ክርክር ማድረግ እና ትችት ማቅረብን ጨምሮ በምርጫ እና በሕዝብ አስተዳደር ጉዳዮች ከወንዶች እኩል የመሳተፍ መብትን የተመለከቱ ጉዳዮች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ኢሰመኮ በ6ተኛው ቀሪ እና ድጋሚ ሀገራዊ ምርጫ ላይ ባደረጋቸው ክትትሎች የተለዩ እምርታዎች እና አሳሳቢ ጉዳዮች በመድረኩ የቀረቡ ሲሆን መልካም አፈጻጸም የታየባቸውን ጉዳዮች ማጠናከር እና አሳሳቢ ተብለው የተለዩ ጉዳዮችን በመቅረፍ በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሴቶች በእኩልነት እና ከአድልዎ በጸዳ መልኩ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ በአጽንኦት ተገልጿል።

በውይይቱ በሴቶች አመራርነት ላይ የተዛቡ አመለካከቶች መኖር፣ በኢኮኖሚ ራስን አለመቻል፣ ከትምህርት ዝግጅት እና ከመረጃ አንጻር የሚታዩ ክፍተቶች እንዲሁም ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ በበይነ መረብ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ሴቶች በሕዝብ አስተዳደር ጉዳዮች ላይ በቂ ተሳትፎ እንዳያደርጉ ተግዳሮት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ መሆናቸው ተመላክቷል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥርዐተ- ጾታ እና ማኅበራዊ አካታችነት የሥራ ክፍል ኃላፊ ክብረዓለም ንጉሴ እና የሕግ ጉዳዮች ባለሙያ የአብስራ ተፈሪ በምርጫ ወቅት ከፖለቲካ ፓርቲ እጩዎች፣ ከግል ተወዳዳሪዎች እና ጋዜጠኞች የሚጠበቅ ኃላፊነት እና ሥነምግባር፣ የሴቶችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ በቦርዱ በኩል የተወሰዱ የሕግ እና የአሠራር ማሻሻያዎች እንዲሁም ቦርዱ አቤቱታዎችን እና ቅሬታዎችን የሚያስተናግድበትን ሂደት አስመልክቶ ለተሳታፊዎች ገለጻ አድርገዋል።

የኢሰመኮ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር መቅደስ አመኑ ሴቶች በሕዝብ አስተዳደር ጉዳዮች ውስጥ ያላቸውን ሚና በማንሳት ሴት የፖለቲካ አመራሮች፣ አባላቶች እንዲሁም ሴት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በምርጫ እና በሕዝባዊ መድረኮች ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያድርጉ አስቻይ ሁኔታን መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል። አክለውም በ7ተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሴቶችን እኩል ተሳትፎ ለማረጋገጥ መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።