የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)የሽግግር ፍትሕን የተመለከተ የሁለት ቀናት የአሰልጣኞች ስልጠና መጋቢት 8 እና 9 ቀን 2018 ዓ.ም. ለሰብአዊ መብቶች ትምህርት ሥራ ክፍል ባልደረቦች በቢሾፍቱ ከተማ ሰጥቷል። ስልጠናው በተለይ የሥራ ክፍሉ አሰልጣኞች በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ ያላቸውን ዕውቀት ለማዳበር ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን የሥራ ክፍሉ ባልደረቦች የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እና ባለድርሻ አካላትን ለማሰልጠን የሚያስፈልጋቸውን የላቀ ሙያዊ ብቃት እንዲላበሱ ለማስቻል ዓላማ አድርጎ የተዘጋጀ ነው።

የሰብአዊ መብቶች ትምህርት ክፍል ባልደረቦች ጠንካራ የሽግግር ፍትሕ መሠረታዊ ዕውቀት ያላቸው በመሆኑ፣ ይህ የአሰልጣኞች ስልጠና ትኩረቱን ያደረገው በመሠረታዊ የንድፈ-ሐሳብ ዕውቀት እና በሽግግር ፍትሕ አተገባበር መካከል ያለውን ክፍተት ከመሙላት አንጻር በአካባቢያዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ውስጥ ባሉ የሽግግር ፍትሕ ሂደት አተገባበር ውስብስብ ጉዳዮች ላይ ነው። ዋና ዋና የሥልጠናው ርዕሰ ጉዳዮችም የዐውድ ሁኔታዎች እና የሰላም ስምምነቶች የሽግግር ፍትሕ ሂደትን እንዴት እንደሚያንጹ መተንተን፣ እንዲሁም በእውነት ፍለጋ፣ በምሕረት እና ተጠያቂነትን የማስፈን ሂደት መካከል ያለውን መስተጋብር እና ግንኙነት ለመረዳት የተለያዩ የሽግግር ፍትሕ ሞዴሎችን መመርመርን ያካተቱ ናቸው። ሥልጠናው ባሕላዊ የፍትሕ ሥርዓቶች በሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ የሚኖራቸውን ሚና እና ከሌሎች የፍትሕ ሂደቶች ጋር የሚቀናጁበት ሁኔታ ላይ ውይይቶችን ያካተተ ነበር። በተጨማሪም የብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት የሽግግር ፍትሕ ሂደትን በመከታተልና ጥሰቶችን በመመዝገብ ረገድ ያላቸውን ልዩ ሚና ዳስሷል።

በተጨማሪም ኢሰመኮ በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ በሚያከናውናቸው ተግባራት ላይ ያተኮረ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ በዚህም ኮሚሽኑ ለመንግሥት ምክረ-ሐሳቦችን በመስጠት፣ የተጎጂዎች እና ተጋላጭ ማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳትፎ ስትራቴጂ ዝግጅት ሂደት ላይ ድጋፍ በማድረግ፣ እና ከሽግግር ፍትሕ ሂደት ጋር የተያያዙ ሂደቶችን ተከታትሎ ምክረ ሐሳቦችን በመስጠት ረገድ እያከናወነ ያለው ሥራ ተብራርቷል። የኢሰመኮ የቀጣይ ተግባራቱ አካል የሆኑትን የተጎጂዎች የመረጃ ቋት (victims database) ማደራጀት፣ ስለ ጊዜያዊ ማካካሻ (interim reparations) ጥናት ማካሄድ፣ እንዲሁም በሽግግር ፍትሕ ሂደት እና እንደ ተፈናቃዮች፣ ሴቶች፣ እና አካል ጉዳተኞች ባሉ የትኩረት መስኮች ያሉ ቁርኝቶች ላይ የሚያተኩሩ መመሪያዎችን (toolkits) ማዘጋጀትን ያሉ ተግባራት ላይ ገለጻ ተደርጓል።

ይህ የሁለት ቀናት የአሰልጣኞች ስልጠና በባለሙያዎች የሚመሩ ገለጻዎችን እና የልምድ ልውውጦችን ያካተተ እና የተሳታፊ መር የሥልጠና ዘዴን የተከተለ ነበር። ሥልጠናው ውስብስብ ንድፈ-ሐሳቦችን ከሀገራዊ ሁኔታዎች ጋር በማዛመድ በተግባራዊ ልምምዶች እና በቡድን ውይይቶች የታገዘ ነበር። በተጨማሪም፣ ስለ ዓለም አቀፍ የሽግግር ፍትሕ ሂደቶች ሰፊ ግንዛቤ ለማስፋት እንደ ኡጋንዳ፣ ጋምቢያ እና ደቡብ አፍሪካ ካሉ ሀገራት ተሞክሮዎች ጋር ንጽጽራዊ ትንተና ተደርጓል።

የአሰልጣኞች ስልጠና ተሳታፊዎችም የሥርዓተ-ጾታ ስሜታዊነትን የተላበሱ ስልቶችን እና የተጎጂዎችን ተሳትፎ በሽግግር ፍትሕ ማዕቀፍ ውስጥ የሚከናወኑበትን አካሄዶች፣ የሽግግር ፍትሕ አተገባበር ተግዳሮቶችን፣ እንዲሁም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት በሂደቱ የሚኖራቸው ሚና ላይ ተወያይተዋል።

በሥልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ አሰልጣኞቹ እነዚህን ውስብስብ ርዕሰ ጉዳዮች ለተለያዩ ሰልጣኞች ለማስተላለፍ የሚያስችል ዝግጅት አግኝተዋል። ይህ ተግባር የኢሰመኮ የሥራ ባልደረቦችን ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሽግግር ፍትሕ መስፈርቶች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ የሚያሳድግ ሲሆን፣ ኢሰመኮ በሀገራዊ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ ያለውን አጠቃላይ ሚናም ያጠናክራል።