የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሽግግር ፍትሕ ጽንሰ ሐሳቦች ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማሳደጊያ ዐውደ ጥናት ግንቦት 11 እና 12 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አካሂዷል። በዐውደ ጥናቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ፣ የሽግግር ፍትሕ ፍኖተ ካርታ፣ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱን ለመተግበር የተዘጋጁ ረቂቅ ሕጎች፣ በሽግግር ፍትሕ ሂደት ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ስላላቸው ሚና እንዲሁም በዚህ ረገድ ኢሰመኮ እያከናወናቸው ስላሉ ተግባራት ገለጻዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በውይይቱ ወቅት የሽግግር ፍትሕ ዋና ምሰሶዎች የሆኑት ተጠያቂነት፣ እውነትን ማፈላለግ፣ የተጎጂዎች ካሳ እና ተቋማዊ ማሻሻያዎች ለፍትሕ፣ ለእርቅ እና ለዘላቂ ሰላም ያላቸው አስተዋጽዖ ላይ ውይይት ተደርጓል። በተጨማሪም የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ውጤታማ እና ተዓማኒ እንዲሆን ግልጽ የትግበራ ሥርዓቶች፣ የተቋማት ቅንጅት እና ጠንካራ እና ገለልተኛ ተቋማት መኖራቸው ለሽግግር ፍትሕ ውጤታማነት ወሳኝ መሆናቸው፤ ረቂቅ ሕጎቹም ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕጎችና መርሖች ጋር ተጣጥመው ሊዘጋጁ እንደሚገባ እንዲሁም ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት በሂደቱ ላይ የሚያከናውኑት የክትትል ሚና ሊጠናከር እንደሚገባ ተገልጿል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ዐውደ ጥናቱ በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረጉን ገልጸው ሂደቱን በውጤታማነት ለመደገፍ የሚያስችል ጠንካራ ተቋማዊ ዐቅምን ለመገንባት መሰል ተከታታይ የግንዛቤ ማሳደጊያ ስልጠናዎች አስፈላጊ መሆናቸው ተገልጿል።

ኢሰመኮ የሠራተኞቹን ዐቅም ለማጎልበት መሰል የግንዛቤ ማሳደጊያ ስልጠናዎችን በቀጣይነት እንደሚያካሂድ እንዲሁም የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ውጤታማ፣ ተዓማኒ እና ሰብአዊ መብቶችን ማዕከል ያደረገ እንዲሆን ለማድርግ አበክሮ እንደሚሠራ አስታውቋል።