የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በትግራይ ክልል እየተፈጸመ ያለውን ወጣቶችን በግዳጅ ወደ ውትድርና የማሰማራት፣ በሐሳብና አስተያየት ነጻነት ላይ የሚደረጉ ገደቦችን፣ እንዲሁም ክልሉን ከሌሎች ክልሎች ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች የሚታዩ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችና ግጭቶች ያስከተሏቸውን አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎች በቅርበት በመከታተል ላይ ይገኛል።

ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል ክልሉ “የትግራይ ሕዝብን ሕልውና ለመጠበቅ” በሚል ርዕስ ወጣቶችን በግዳጅ ወደ ውትድርና የማሰማራት የውሳኔ ሰነድ (“ሕግ”) ማውጣቱንና ሥራ ላይ ማዋሉን ለመገንዘብ ችሏል። የውሳኔ ሰነዱ የወጣው በ2012 ዓ.ም. ምርጫን ለማካሄድ ሕገ መንግስታዊ ተቋም ከሆነው የምርጫ ቦርድ እውቅና ውጪ በክልሉ ተደርጎ በነበረው ምርጫ መሠረት የተቋቋመ፤ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የፈረሰ የ“ምክር ቤት” አባላት በድጋሚ በመሰብሰብ መሆኑን ኢሰመኮ ለመረዳት ችሏል። ይህ ተግባር የፕሪቶሪያን ስምምነት የሚጥስ ከመሆኑም ባሻገር በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ (ኢ.ፌ.ዴ.ሪ) ሕገ መንግሥት አንቀጽ 51 እና 52 መሠረት ለፌዴራል መንግሥትና ለክልሎች የተሰጠውን የሥልጣን ክፍፍል የሚጻረር እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55(7) መሠረት የሀገርና የሕዝብ መከላከያ፣ ደኅንነትና የፖሊስ ኃይል አደረጃጀትን እንዲሁም መሠረታዊ የሰዎች ሰብአዊ መብቶችና የሀገር ደኅንነት ጉዳዮች የመወሰን ኃላፊነትን በተመለከተ የተደነገገውን የሚጻረር ነው።

ከሰኔ 17 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጻሚ መደረግ ጀምሯል የተባለው ይህ የግዳጅ ውትድርና ሰነድ የክልሉ ተወላጅ የሆነ ማንኛውም ሰው ለግዳጅ ውትድርና የሚቀርብለትን ጥሪ የመቀበል ግዴታ እንዳለበት የሚደነግግ ሲሆን ጥሪውን የማይቀበል ሰው ከብር 10,000 እስከ ብር 50,000 እንደሚቀጣ ይደነግጋል። በተጨማሪም በክልሉ ውስጥም ሆነ ከክልሉ ውጪ ሆነው ሕዝቡ ድርጊቶቹን እንዳይደግፍ የሚያደርጉ ተግባራትን የሚፈጽሙ ወይም በክልሉ የተላለፉ ውሳኔዎችን የሚተቹ ወይም የሚቃወሙ ግለሰቦች ወደ ኃላ ጭምር በመመለስ ከ5 እስከ 25 ዓመት ጽኑ እስራት እና በንብረት መወረስ እንደሚቀጡ ይደነግጋል። የጸጥታ አካላት ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ግለሰቦችን እንዲይዙና ፍተሻ እንዲያካሂዱ ሥልጣን የሚሰጥ ድንጋጌንም ያካተተ መሆኑን ኢሰመኮ ለመገንዘብ ችሏል።

ሕፃናትን እና ሌሎች ለመብቶች ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን በግዳጅ ለወታደራዊ ምልመላ ወይም ለጦርነት ማሰማራት የሕገ መንግሥቱንና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች መርሖችና ድንጋጌዎችን እንዲሁም በ1949 የጄኔቫ ስምምነቶች የጋራ አንቀጽ 3 እና በዓለም አቀፍ ልማዳዊ ሰብአዊነት ሕግ የተደነገጉ መርሆዎችን የሚጥስ ነው። ይህ ተግባር ከመንግሥት ውጪ ባለ ታጣቂ ቡድን የሚፈጸም በመሆኑ፣ እንደ ጉልበት ብዝበዛ ብሎም እንደ የጦር ወንጀል ሊቆጠር የሚችል ነው። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 17 እና 18 ማንኛውም ሰው በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጪ ነጻነቱን ሊያጣ ወይም ሊያዝ እንደማይችል እንዲሁም በግዳጅ ወይም በኃይል ሥራ እንዲሠራ ሊገደድ እንደማይችል ይደነግጋሉ። ከዚህ በተጨማሪ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ጸድቆ የወጣውንና ኢትዮጵያ በአዋጅ ቁጥር 826/2006 አጽድቃ የሕጓ አካል ያደረገችውን የሕፃናት መብቶች ስምምነት አማራጭ ፕሮቶኮል የሆነውና ሕፃናት በትጥቅ ግጭት ውስጥ ስለሚኖራቸው ተሳትፎ የሚመለከተው ስምምነት በአንቀጽ 4 የታጠቁ ቡድኖች ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን በማንኛውም ሁኔታ ለወታደራዊ አገልግሎት መመልመልም ሆነ በትጥቅ ግጭት ውስጥ መጠቀም እንደማይገባቸው ይደነግጋል።

በአህጉራዊ ደረጃ በግጭት አውድ ጭምር ተፈጻሚ በሆነው የአፍሪካ ሕፃናት መብቶችና ደኅንነት ቻርተር አንቀጽ 22፣ አባል ሀገራት ሕጻናት በትጥቅ ግጭቶች ውስጥ በቀጥታ እንዳይሳተፉና ማንኛውም ሕጻን ለወታደራዊ አገልግሎት እንዳይመለመል ሁሉንም አስፈላጊ እርምጃዎች የመውሰድ ግዴታ ያለባቸው መሆኑና በትጥቅ ግጭት ተጽዕኖ ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያገኙ ሁሉንም የሚቻሉ እርምጃዎች እንዲወስዱ ግዴታ ይጥላል።

የግዳጅ ውትድርና ሰነዱንና ሌሎች ውሳኔዎችን በሰላማዊ መንገድ የሚተቹ ወይም የሚቃወሙ ግለሰቦች በከባድ እስራት እንደሚቀጡና ንብረታቸው እንደሚወረስ የተደነገገ ሲሆን ይህም ዜጎች ሐሳባቸውን በነጻነት እንዳይገልጹ፣ በሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አስተያየት እንዳያካፍሉ እና በፍርሃት ውስጥ እንዲኖሩ በማድረግ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 እና በሌሎች ኢትዮጵያ ተቀብላ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተረጋገጠውን የሐሳብና አስተያየት ነጻነት፣ የሚዲያ ነጻነትና መረጃ የማግኘትና የማሰራጨት መብት ጋር የሚቃረን ነው።

በክልሉ ከዚህ የግዳጅ ውትድርና ሰነድ መውጣት አስቀድሞም በተለያዩ አካባቢዎች ወጣቶችን፣ በተለይም ሕጻናትን፣ ተፈናቃዮችን፣ የአእምሮ ጤና ሕሙማንን፣ እንዲሁም ከስደተኛ ካምፖችና ከጸበል ሥፍራዎች ጭምር በግዳጅ በማሰባሰብ ወደ ወታደራዊ ሥልጠና ካምፖች የማስገባት ተግባር ሲፈጸም የነበረ ሲሆን የግዳጅ ውትድርና ሰነዱ ከወጣ በኋላም ይህ ተግባር ይበልጥ ተጠናክሮ ቀጥሎ የአብነት ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ከአብያተ ክርስትያናት፣ እንዲሁም በርካታ ሌሎች ሰዎችን ከገበያ ስፍራ፣ ከወጣቶች ማዘውተሪያ ማዕከላት እና ቤት ለቤት በሚደረግ አሰሳ በማፈስ ወደ ወታደራዊ ተግባር እንዲሰማሩ ማድረግ መቀጠሉን ኢሰመኮ ታፍሰው ከተመለሱ ወጣቶች፣ ከቤተሰቦቻቸው እና ከተለያዩ ሰነዶች ባሰባሰበው መረጃ ማረጋገጥ ችሏል። በግዳጅ ከሚታፈሱ ሰዎች መካከልም በአብዛኛው እድሜያችዉ ከ18 ዓመት በታች መሆናቸዉን ኢሰመኮ ለማረጋገጥ ችሏል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በክልሉ እና በአጎራባች ክልሎች በታጠቁ ኃይሎች መካከል የተከሰቱ ግጭቶችም በሲቪል ሰዎች ሕይወትና ንብረት ላይ እያስከተሉ ያሉት ጉዳቶች አሳሳቢ መሆናቸውን ለመገንዘብ ተችሏል። ለአብነት ያህል፣ ግንቦት 17 እና 18 ቀን 2018 ዓ.ም. በሰሌንውሃ ቀበሌ በተከሰተ ግጭት አባትና ልጅ የሆኑ ሁለት ሲቪል ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውንና በአካባቢው በሚገኙ ከብቶች ላይ ጉዳት መድረሱን ኢሰመኮ አረጋግጧል። በተጨማሪም በጥር ወር 2018 ዓ.ም. በተከሰቱ ውጥረቶችና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ምክንያት ከሰሜን ምዕራብ ዞን ፀለምቲና ላዕላይ ፀለምቲ ወረዳዎች፣ ማይ ፀብሪ ከተማ፣ ከደቡብ ምሥራቅ ዞን ዒስራ ዓዲ ወጀራት ወረዳ፣ እንዲሁም ከደቡባዊ ዞን ራያ ጨርጨርና ራያ አላማጣ በርካታ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ያለ በቂ የምግብና የመጠለያ ድጋፍ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ኢሰመኮ አረጋግጧል። በተመሳሳይ ሰኔ 18 ቀን 2018 ዓ.ም. በአፋር ክልል አብዓላ ከተማ አስተዳደር ሙርጋ ቀበሌ ውስጥ ልዩ ስሙ “አሳልጌ” በተባለ ሥፍራ ጥቃት ተፈጽሞ በነዋሪዎችና በግመሎች ላይ ጉዳት መድረሱን እንዲሁም በርካታ የሙርጋ ቀበሌ ነዋሪዎች ከአካባቢው መፈናቀላቸውን ኢሰመኮ ተረድቷል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ይህ በትግራይ ክልል የሚስተዋለው የፖለቲካ ውጥረትና ወታደራዊ እንቅስቃሴ ከፕሪቶሪያ የተኩስ አቁምና የዘላቂ ሰላም ስምምነት በኋላ በክልሉ የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት ወደ ኋላ የሚመልስ፣ የስምምነቱን ተፈጻሚነት የሚጥስ እና ለተጨማሪ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መንስኤ መሆኑ ታውቆ፣ በክልሉ የሚንቀሳቀሰውን ታጣቂ ኃይል ጨምሮ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ውጥረትንና ግጭትን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ፣ የሰብአዊ መብቶችን በተሟላ ሁኔታ እንዲያከብሩ እና የፖለቲካ ልዩነቶችን በውይይት፣ በምክክርና በሕግ አግባብ በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም በቅርቡ በክልሉ ወጣ የተባለው የግዳጅ ውትድርና ሰነድ ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ፣ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የሌለው እና ለተደራራቢና ከፍተኛ ለሆነ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምክንያት በመሆኑ በአስቸኳይ ተፈጻሚነቱ እንዲቆም አሳስበዋል።