የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃ ለማድረግ እና ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት በተያዙ እቅዶች፣ አስቻይ ሁኔታዎች እና ተግዳሮቶች ላይ ሰኔ 18 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
የምክክር መድረኩ ከRegional Durable Solutions Secretariat (ReDSS)፣ Lutheran World Federation (LWF) እና ከEthiopia Conflict Sensitivity Hub (ECSH) ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የሰላም ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ተወካዮች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ተወካዮች እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የዓለም ባንክ እና ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃ እና ድጋፍ የሚያደርጉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

በመድረኩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እና የዘላቂ መፍትሔ አተገባበር አሁናዊ ሁኔታን አስመልክቶ በኢፌ.ዴ.ሪ የሰላም ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን ለተሳታፊዎች ሰፊ ገለጻ ተደርጓል። የሀገር ወስጥ ተፈናቃዮች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ በመሆኑ የፌዴራል መንግሥት ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎች ከክልሎች ጋር በመተባበር ድጋፍ የማድረግና በዘላቂነት የማቋቋም ኃላፊነት እንዳለበት ተገልጿል። በተጨማሪም መፈናቀልን ለመከላከል እና ከተፈናቃሉም በኋላ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ፖሊሲዎች እና የሕግ ማዕቀፎች ቢኖሩም በሰላም እና ደኅንነት እጦት፣ በማኅበራዊ አገልግሎቶች አለመሟላት እንዲሁም ቅንጅት እና ቁርጠኝነት ማነስ ምክንያት የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ በመድረኩ ተብራርቷል። ከምግብ አቅርቦት ባለፈ ተፈናቃዮችን እንደ ምርጫቸው በዘላቂነት ለማቋቋም ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ በመሆኑ ክልሎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ተጠይቋል።


በሌላ በኩል በመድረኩ የተሳተፉ የክልል አደጋ ሥጋት አመራር ኃላፊዎች፣ በየክልሎቻቸው የተሠሩ የዘላቂ መፍትሔ ሥራዎችን እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን አጋርተዋል። በዚህም በአፋር፣ በአማራ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በማእከላዊ ኢትዮጵያ እና በሐረሪ ክልሎች የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለመደገፍ ጥረቶች ቢኖሩም በጸጥታ ችግር እና በክልሎች መካከል ባለው ደካማ ግንኙነት ምክንያት ከሚያስተዳድሩት ክልል ውጭ ተፈናቅለው ለሚገኙ ዜጎች ዘላቂ መፍትሔ መስጠት እንዳልተቻለ አስረድተዋል። በመሆኑም በላኪና ተቀባይ ክልሎች መካከል መተማመን እንዲፈጠር በግልጽ አጀንዳ ላይ መወያየት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ተወካዮች በበኩላቸው፣ መፍትሔ ሳያገኙ ለዓመታት በመጠለያ ጣቢያዎች እና በተቀባይ ማኅበረሰብ ተጠልለው በመቆየታቸው ለከፋ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ሥነ-ልቦና ችግር መጋለጣቸውን ገልጸዋል። ለተፈናቃዮች የሚደረገው ሰብአዊ ድጋፍ ሕይወትን ለማቆየት አስፈላጊ ቢሆንም ዋና ምርጫቸው ግን በዘላቂነት ተቋቁመው፣ ሠርተው እና አምርተው ራሳቸውን ማስተዳደር በመሆኑ መንግሥት ዘላቂ መፍትሔ እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል።

የኢሰመኮ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ ስደተኞች እና ፍልሰተኞች መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ምሕረተአብ ገብረመስቀል፣ ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በውይይት የጋራ መግባባት ላይ መድረስ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። አክለው በኢሰመኮ በኩል ወደ ፊት መሰል ውይይት እና የምክክር መድረኮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በመጠቆም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸው በአግባቡ እንዲወጡ ጠይቀዋል።