በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና Tomorrow is Better በተባለ ሀገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ሰብሳቢነት የሚመራው “የኢሰመኮ-ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የትብብር መድረክ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች ንዑስ ቡድን” ትብብራቸውን ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ሰኔ 22 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ውይይት አድርገዋል። በመድረኩ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ከአፋር እና አማራ ክልሎች የተውጣጡ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ ስደተኞች እና ፍልሰተኞች መብቶች ጉዳይ ላይ የሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተሳትፈዋል።

በውይይቱ የተፈናቃዮች አያያዝን በሚመለከት የተሟላ የሕግ ማዕቀፍና ተቋማዊ አደረጃጀት አለመኖር፣ መፈናቀልን በመከላከል ረገድ ክፍተት መኖር፣ እንዲሁም የሰብአዊ ድጋፍ እጥረትና የዘላቂ መፍትሔ አተገባበር ተግዳሮቶች ተጠቅሰዋል። በሌላ በኩል፣ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ከምዝገባ፣ ከሰነድ አሰጣጥ፣ የመንቀሳቀስ ነጻነትና የመሥራት መብቶች መከበር አንጻር የሚገጥሟቸው ክፍተቶች የተዳሰሱ ሲሆን፤ መደበኛ ባልሆኑ የጉዞ መስመሮች ድንበር አቋርጠው በሚጓዙ ፍልሰተኞች ላይ እየደረሰ ያለው አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታም ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
በመድረኩ በ2019 በጀት ዓመት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው በቅንጅት ሊሠሩ በታቀዱ ዋና ዋና ተግባራት ላይ ስምምነት ላይ ተደርሷል። እንዲሁም የትብብር መድረኩን የበለጠ ውጤታማ ማድረግና በየጊዜው የመረጃ ልውውጥ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደርጓል።

የኢሰመኮ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ ስደተኞች እና ፍልሰተኞች መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር እና በትብብር መድረኩ በመፈናቀል ዐውድ ያሉ ሰዎች ንዑስ ቡድን ሰብሳቢ ምሕረተአብ ገብረመስቀል፤ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ ስደተኞች እና ፍልሰተኞች መብቶች በተገቢው ሁኔታ እንዲስፋፉ፣ እንዲከበሩ እና እንዲጠበቁ የማድረግ ዓላማ በአንድ ተቋም ብቻ እውን ሊደረግ እንደማይችል ገልጸዋል። አክለውም ለዚህ ዓላማ መሳካት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዋና አጋሮች መሆናቸውን በማስታወስ፤ ወደፊት በቅንጅት ሊሠሩ የታሰቡ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የትብብር መድረኩን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።