የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሽግግር ፍትሕ ትግበራን ለመከታተል ባዘጋጀው ረቂቅ የክትትል ማዕቀፍ ላይ ሐምሌ 13 እስከ 17 ቀን 2018 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዐውደ ጥናት አካሂዷል። ዐውደ ጥናቱ ኢሰመኮ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱን ለመከታተል ያለውን ተቋማዊ አቅምና ዝግጁነት ለማጠናከር ያለመ ሲሆን፣ ከኢሰመኮ ዋናው መሥሪያ ቤትና ከከተማ ጽሕፈት ቤቶች የተውጣጡ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

በኢትዮጵያ የብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ቀረጻና የማስፈጸሚያ ዕቅድ ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ትግበራ የተገባ ሲሆን የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ፣ አካታች እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መሥፈርቶችን ያሟላ መሆኑን ለማረጋገጥ ገለልተኛ ክትትል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ በዐውደ ጥናቱ ተመላክቷል። ከዚህ አንጻር የተዘጋጀው ረቂቅ የክትትል ማዕቀፍ ኢሰመኮ የሂደቱን ተአማኚነትና ፍትሐዊነት እንዲሁም ከሕገ-መንግሥቱና ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎችና መሥፈርቶች ጋር የተጣጣመ መሆኑን በቅርበት ለመከታተል እንደሚረዳ በውይይቱ ተነስቷል።

በዐውደ ጥናቱ ላይ የመድረኩ ተሳታፊዎች በብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ይዘት፣ እስካሁን በተከናወኑ ተግባራት፣ በኢሰመኮ ስልታዊ ሚና፣ በረቂቅ የክትትል ማዕቀፉ እንዲሁም በክትትሉ መርሖችና መስፈርቶች ላይ ሰፊ ትንተና እና ውይይት አድርገዋል። በተጨማሪም የኢሰመኮ የተለያዩ የሥራ ክፍሎች የሚተገብሯቸውን የክትትል ዘዴዎች፣ የሪፖርት አቀራረቦች፣ መለኪያዎች እና አመልካቾችን ልምድ በመለዋወጥ ረቂቅ የክትትል ማዕቀፉን ይበልጥ ለማዳበር ተችሏል።

የኢሰመኮ የዋና ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ቃልኪዳን ደረጀ  በዐውደ ጥናቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢሰመኮ በሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ ያለውን ገለልተኛ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሚና ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ረቂቅ የክትትል ማዕቀፉ የኢሰመኮን ተልዕኮ በአግባቡ የሚያንጸባርቅ፣ የሁሉም የሥራ ክፍሎች ልምድና እውቀትን ያካተተ፣ እንዲሁም በሂደቱ ላይ ወጥ የሆነና በማስረጃ የተደገፈ ክትትል ለማከናወን እና ሪፖርት ለማድረግ የሚያስችል መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።