የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር፣ የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጣናዊ ጽሕፈት ቤት (OHCHR-ESARO) ጋር በመተባበር መስከረም 28 እና 29 ቀን 2019 ዓ.ም. ለተጎጂዎች ማኅበራት ተወካዮች የዐቅም ግንባታ እና የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ አካሂዷል። በመድረኩ ከአፋር፣ ከአማራ፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ከጋምቤላ፣ ከሐረሪ፣ ከሶማሊ እና ከትግራይ ክልሎች የተውጣጡ 44 የተጎጂዎች ማኅበራት ተወካዮች ተሳትፈዋል። 

የዚህ ስልጠና ዓላማም የተጎጂዎች ማኅበራት በሥነ-ምግባር እና የሰብአዊ መብቶች ደረጃዎችን ታሳቢ ያደረገ የተጎጂዎች ልየታ (victim mapping) እና መረጃን የማሰባሰብ (documentation) ዐቅማቸውን ማጠናከር ሲሆን፤ በተጨማሪም ተሞክሮዎችን የሚለዋወጡበትን፣ ትብብራቸውን የሚያጠናክሩበትን እንዲሁም በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ ለሚኖራቸው ተሳትፎ ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ጉዳዮች በግልጽ የሚያስቀምጡበትን መድረክ ማመቻቸት ነው። 

በሚያዝያ 2016 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ መጽደቁን ተከትሎ፣ የተጎጂ ማኅበራት ተጎጂዎችን በመለየት (victim mapping)፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትቶችን መረጃ በማሰባሰብና በማደራጀት (documentation)  እና የተጎጂዎች የመረጃ ቋት በማዘጋጀት ሂደት ውስጥ የተጎጂዎች ማኅበራት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ለማበርከት ከፍተኛ ተነሳሽነት አሳይተዋል። ሆኖም በርካታ ማኅበራት የቴክኒክ ዐቅም ውስንነት፣ ደረጃውን የጠበቀ የሰነድ አያያዝ ሥርዓት አለመኖር፣ እንዲሁም የተጎጂዎችና ከጉዳት ያገገሙ የጥቃት ሰለባዎች( survivors) ደኅንነት፣ ግላዊነት እና ሥነ-ልቦና አስመልክቶ የተለያዩ ተግዳሮቶች ሲያጋጥማቸው ቆይቷል። እነዚህ ተግዳሮቶች መረጃ የማሰባሰብ( documentation) ሥራው አግባብነት ያልቸው የሰብአዊ መብቶች ደረጃዎች አንጻር እና ከሥነ-ምግባር መርሖች ጋር በተጣጣመ መልኩ መከናወኑን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ያሳያሉ።  

በሥነ-ምግባራ የተመሠረተ የተጎጂዎች ልየታ እና መረጃ ማሰባሰብና ማደራጀት የተጎጂዎችን እውነትን የማወቅ፣ ፍትሕን፣ ውጤታማ መፍትሔ እና ካሳን የማግኘት መብቶችን  ለማስከበር ወሳኝ ናቸው።በተጨማሪም የተጎጂዎችን ግላዊነት እና ደኅንነት ለመጠበቅ፣ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል እንዲሁም መረጃዎች አግባብነት ባላቸው የሽግግር ፍትሕ ተቋማት ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖራቸውና በኃላፊነት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ያስችላል። በመሆኑም ወጥ የሆነና ተጎጂ-ተኮር ዘዴዎችን( victim-centred approach) መተግበር የመረጃ ማሰባሰብና ማደራጀት (documentation)  ጥረቶች የተጎጂዎችን እና ከጉዳት ላገገሙ የጥቃት ሰለባዎች( survivors) ክብርና መብቶች መጠበቃቸውን ለማረጋገጥ አስፈላጊ ነው። 

በመድረኩም ኢሰመኮ ያዘጋጀውን የተጎጂዎች ልየታ እና  የመረጃ ማሰባሰብና ማደራጀት መመሪያ  ያስተዋወቀ ሲሆን፣ ሥነ-ምግባራዊ እና የሰብአዊ መብቶች ደረጃዎችን ያከበረ የመረጃ ማሰባሰብና ማደራጀት ሥራ ዓላማዎች፣ ሥነ ዘዴዎች እና መመዘኛዎች ለተሳታፊዎች ቀርቧል። የሶማሊ ክልል የተጎጂዎች ማኅበራት ተወካዮች የተጎጂዎችን መረጃ የመሰብሰብና የመለየት ሂደት ልምዳቸውን አጋርተዋል። ተሳታፊዎችም በተጎጂዎች ልየታ አሠራሮች እና አግባብነት ባላቸው የሰብአዊ መብቶች ደረጃዎች ላይ በቡድን ተወያይተው የውይይታቸውን ውጤት አቅርበዋል። 

ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት (OHCHR) የመጡ ባለሙያዎችም በተጎጂ ማኅበራት  ሥራዎች ውስጥ ሥርዓተ-ጾታን ያማከሉ  ምላሾች እና የሥነ-ልቦና ድጋፎች (trauma-informed approaches) መካተት እንዳለበቸው አንስተዋል።  በውይይቱም ሴት ተጎጂዎችን በተለይም ከግጭት ጋር የተያያዙ የጾታዊ ጥቃት ሰለባዎችን( survivors) ልዩ ፍላጎቶችና ልምዶችን ታሳቢ ማድረግ በሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፏቸውን ለማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑ ተነስቷል። 

የተጎጂዎች ማኅበራትን፣ ከአዲስ አበባ ከተማ የተውጣጡ 30 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና የመንግሥት ተቋማት ተወካዮችን ያገናኘው ይህ መድረክ፣ የተጎጂዎች ማኅበራት አመሰራረት፣ እድገት፣ ያስመዘገቧቸውን ስኬቶች እና ያሉባቸውን ቀጣይ ተግዳሮቶች ለማጋራት እድል ፈጥሯል። በተጨማሪም የተጎጂዎች ማኅበራት ጥምረት ዓላማውንና የድርጊት መርኅ ግብሩን አቅርቦ አግባብነት ካላቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሊደረጉ የሚገቡ የድጋፍና የትብብር መስኮችን አመላክቷል። 

በሌላ በኩል መድረኩ የተጎጂዎች ማኅበራት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ያላቸውን ቅንጅት ለማጠናከር፣ የተጎጂዎችን ተነሳሽነት ለመደገፍ እና በሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ውስጥ ይበልጥ የተዋቀረ ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂያዊ ውይይት የተደረገበት ነበር። የተጎጂዎች ልምዶች፣ ፍላጎቶች እና ቅድሚያ የሚሰጧቸው ጉዳዮች በሽግግር ሂደቱ ውስጥ ይበልጥ እንዲንጸባረቁ ማድረግ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱን ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ አካታችና ትርጉም ያለው እንደሚያደርገውም ተመላክቷል። በውይይቱ ኢሰመኮ የተጎጂዎች ልየታ እና የመረጃ ማሰባሰብና ማደራጀት መመሪያን በማዘጋጀት እንዲሁም በተጎጂዎች የመረጃ ቋት ዝግጅትና ተሳትፎ ዙሪያ ድጋፍ መስጠትን ጨምሮ፣  የተጎጂ ማኅበራትን የቴክኒክ እና የውትወታ ዐቅም ማጠናከሩን  እንደሚቀጥል የገለጸ ሲሆን፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት (OHCHR)፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና አግባብነት ካላቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበርም የተጎጂዎችን ትርጉም ያለው ተሳትፎ ለማረጋገጥ፣ ሰብአዊ መብቶችን ያከበረ እና ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ የሽግግር ፍትሕ ሂደት እንዲሰፍን ለማድረግ ወሳኝ ሚናውን እንደሚወጣ አረጋግጧል።