- Version
- Download 9
- File Size 44.00 KB
- File Count 1
- Create Date January 30, 2024
- Last Updated April 9, 2024
አንኳር ጉዳዮች:- በሀገር ውስጥ በሴቶችና በሕፃናት የመነገድ ድርጊት የባለግዴታዎች ምላሽ አሰጣጥን በተመለከተ የተደረገ የክትትል ሪፖርት
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በሀገር ውስጥ በሴቶችና በሕፃናት የመነገድ ድርጊት የባለግዴታዎች ምላሽ አሰጣጥ ላይ ያተኮረ ባለ 33 ገጽ የክትትል ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል። ይህ የክትትል ሪፖርት በሀገር ውስጥ በሴቶች እና በሕፃናት መነገድን የመከላከል፣ ለተጎጂዎች የሚደረጉ ጥበቃ እና መልሶ ማቋቋምን፣ የአጥፊዎችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የተወሰዱ እርምጃዎችን እንዲሁም እነዚህን ተግባራት ለመከወን የተዘረጉ የትብብር ማዕቀፎች ከሰብአዊ መብቶች መርሖች እና መመዘኛዎች ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን በመመዘን አንኳር ግኝቶችን እና ምክረ ሐሳቦችን የያዘ ነው።
በሀገር ውስጥ በሰዎች የመነገድ ድርጊት መነሻ፣ መተላለፊያና መዳረሻ ተብለው የተለዩ ቦታዎችን መሠረት በማድረግ በመጀመሪያ ዙር በአማራ ክልል በባሕር ዳር ከተማ እና በአፋር ክልል በሰመራና ሎጊያ ከተሞች፤ በሁለተኛ ዙር በሲዳማ ክልል ሃዋሳ ከተማ እና በቀድሞ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በአሁኑ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት ወላይታ ዞን፣ ከኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሸዋ ዞን፤ በአዳማ ከተማ እና በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ቢሮዎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የፌዴራል ተቋማት ኮሚሽኑ ክትትል አድርጓል። በዚህም 23 የክልል ቢሮዎች፣ 6 የፌዴራል ተቋማት፣ 4 የከተማ አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች፣ 14 የዞን መምሪያዎች እና የፖሊስ ጣቢያዎች፣ 13 መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጀቶች፣ 4 የሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች እንዲሁም 21 የድርጊቱ ተጎጂዎችን ማነጋገር እና የተጎጂ ታሪኮችን መመልከት ተችሏል።
በክትትሉ ሴቶች እና ሕፃናት በሀገር ውስጥ በሰው መነገድ ድርጊት ሳቢያ ከጾታዊ እና አካላዊ ጥቃት እንዲሁም ከአድልዎና መገለል የመጠበቅ መብቶቻቸው፣ የአካልና የአእምሮ ደኅንነት መብት፣ የነጻነትና ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት እና ፍትሕ የማግኘት መብቶቻቸው እንደተጣሱ ተመላክቷል። በሰው መነገድን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጡ ሕጎች፣ ፖሊሲዎች፣ የድርጊት መርኃ ግብሮች፣ መነሻና ሳቢ ምክንያቶችን ለመቀነስ የሚያስችሉ እርምጃዎች እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫና የስልጠና መርኃ ግብሮች ከሁሉን አቀፍ ምላሽ ይልቅ፤ በዋናነት ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና ከሀገር ውጪ በሰው የመነገድ ድርጊት ላይ ብቻ ትኩረት ያደረጉ መሆናቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
በሀገር ውስጥ በሴቶችና በሕፃናት የመነገድ ድርጊት የባለግዴታዎች ምላሽ አሰጣጥን በተመለከተ የተደረገ የክትትል ሪፖርት