- Version
- Download 138
- File Size 9.82 MB
- File Count 1
- Create Date February 21, 2023
- Last Updated August 18, 2023
የአረጋውያን መንከባከቢያ ማእከላት የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ሪፖርት
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በሕግ ከተሰጡት ሥልጣን፣ ተግባርና ኃላፊነቶች መካከል የሰብአዊ መብቶች ክትትል ማድረግ አንዱ በመሆኑ በተለይ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ያደረጉ የክትትል ሥራዎችን ያከናውናል፡፡
አረጋውያን ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዘው ለሚመጡ አድሎዎች እና ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተጋላጭ በመሆናቸው እና የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ለመስጠት ሲባል አረጋውያንን በአንድ ማእከል ውስጥ አሰባስቦ እንክብካቤ መስጠት በኢትዮጵያ እየተለመደ የመጣ ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም ኢሰመኮ በተቋም ውስጥ ለአረጋውያን የሚሰጥ ድጋፍና እንክብካቤ ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መመዘኛዎች እና የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ካወጣው አነስተኛ መስፈርት (minimum standard) አንጻር ለመገምገም፣ በተቋም ውስጥ የሚገኙ አረጋውያን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታን ለማየት እና የተቋማቱን የእንክብካቤ አገልግሎት ደረጃ በመመዘን መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮችን በመለየት ምክረ ሐሳቦችን ለማቅረብ የሚረዳ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የሰብአዊ መብቶች ክትትል በሦስት ክልሎች በሚገኙ አምስት የአረጋውያን መንከባከቢያ ማእከላት ላይ አከናውኗል፡፡
ክትትሉ ከግንቦት 23 እስከ ሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ የተከናወነ ሲሆን፤ እያንዳንዳቸው ሦስት አባላት ያሏቸው 2 የክትትል ቡድኖች ተሠማርተዋል፡፡ በዚህ የክትትል ሥራ ኮሚሽኑ በአጠቃላይ ከ43 ሰዎች ጋር ቃለ መጠይቆችን ያደረገ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 19 ወንዶች፣ 24 ሴቶች እና 22 አረጋውያን ናቸው፡፡ በተጨማሪም ከሰብአዊ መብቶች ክትትሉ መልስ የክትትሉን ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች ለማስተዋወቅ፣ ፈጣን ምላሽ የሚሹ ጉዳዮችን ለይቶ ከማእከላቱ ኃላፊዎች፣ ከሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር፣ በክልል፣ በዞን እና በከተማ/ወረዳ ደረጃ ከሚገኙ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቢሮዎች፣ ከየከተማ አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች እንዲሁም የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበርን ጨምሮ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር የምክክር መድረክ መስከረም 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ተከናውኗል፡፡
ክትትሉ የተከናወነባቸው ማእከላት በኦሮሚያ ክልል የሚገኙት እልፍነሽ የአረጋውያን መንከባከቢያ ማእከል እና ምግባረ ሰናይ የአረጋውያንና የአካል ጉዳተኞች መርጃ ድርጅት፣ በሲዳማ ክልል የሚገኘው ሜሪ ጆይ አረጋውያን ማእከል - ሃዋሳ ቅርንጫፍ እንዲሁም በአማራ ክልል የሚገኙት አጣዬ የአረጋውያንና ምስኪኖች መርጃ ማእከል እና ሀበሻ የአረጋውያንና ምስኪኖች መርጃ ማኅበር ናቸው፡፡ በማእከላቱ የሚገኙ አረጋውያን ዝርዝር መረጃ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ በሀበሻ አረጋውያን እና ምስኪኖች መርጃ ማኅበር የተከናነወነው ክትትል ተጨማሪ ምርመራ የሚፈልግ በመሆኑ፤ በሌላ ሪፖርት የሚሸፈንና ይፋ የሚደረግ ይሆናል፡፡