On International Day of Disabled Persons, Rigbe Gebrehawaria Hagos, Ethiopian Human Rights Commission’s Commissioner for Disability Rights and the Rights of Older Persons, calls on private and government employers to allocate resources for reasonable accommodation to ensure the right to work of people with disability.
የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን "አካታች የፈጠራ ሥራና ሽግግራዊ መፍትሔ ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተደራሽነት" በሚል መሪ ቃል የሚታሰብ ሲሆን፣ መሪ ቃሉ በተለይም የቴክኖሎጂ እና ሌሎች ፈጠራዎች አካባቢን እና አጠቃላይ የአካል ጉዳተኞችን አኗኗር አካታች እና ተደራሽ በማድረግ ረገድ ያላቸውን ከፍተኛ ሚና ለማጉላት ያለመ ነው። አካል ጉዳተኞች በግል እና በቤተሰባቸው የሚገጥሟቸውን ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ከሚደረገው ጥረት ባሻገር፣ ለሁሉም ሕዝብ ተደራሽ ሊሆኑ ከሚገባቸው አገልግሎት ሰጪ አካባቢዎች እና ተቋማት አካል ጉዳተኞችንም ሙሉ በሙሉ የሚያካትቱ እና ለእነሱ ተደራሽ ሊሆኑ ይገባል። ለምሳሌ የትራንስፖርት ሰጪ አውቶብሶች መግቢያ እና መውጫዎች ወደ መሬት ዝቅ ማለት የሚችሉ እንዲሆኑ በማድረግ፣ በጽሑፍ እና በቀስት አቅጣጫ አመላካቾችን በሕንጻዎችና በመንገዶች ላይ በመለጠፍ ወይም ሊፍቶች በአግባቡ መስራታቸውን እና የድምጽ አቅጣጫ መጠቆሚያ እንዲኖራቸው በማድረግ አገልግሎት ሰጪ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። በሥራው ዓለም ደግሞ አካል ጉዳተኞች በተሟላ መልኩ እንዲካተቱ ለማድረግ እና በሙያቸው መሳተፍ እንዲችሉ የሚያስችሉ ኮምፕዩተሮች፣ አፕሊኬሽኖች፣ ስልኮች እና ሌሎች በርካታ አጋዥ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ያሉ ቢሆንም፣ በሀገራችን እነዚህን ማግኘትም ሆነ መሸመት በጣም አዳጋች ነው። አካል ጉዳተኞች በመረጡት ሙያ የመሰማራት ሰብአዊ መብታቸው እንዲረጋገጥ እና እኩልነት እና አካታችነት የሚሉት የሰብአዊ መብቶች መርሆች እንዲከበሩ ማድረግ ይገባል። ይህም የመንግሥት ግዴታ ነው። ሆኖም ለምሳሌ መንግሥታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አሰሪዎችና ድርጅቶች ለአካል ጉዳተኛ ባለሞያዎች ተመጣጣኝ ማመቻቸት (reasonable accommodation) በማድረግ፤ ማለትም ረዳት ባልደረቦች በመቅጠር፣ የሥራ አካባቢን ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ በማድረግ፣ ለዚህም አስፈላጊውን ሃብት በመመደብ ለአካል ጉዳተኞች ምቹና አካታች ዓለም ለመፍጠር አስተዋጽዖ ሊያደርጉ ይችላሉ።