የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከጥር 1 ቀን 2018 ዓ.ም. እስከ መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም. ባለው የበጀት ዓመቱ 3ኛ ሩብ ዓመት በሰብአዊ መብቶች እና በሽግግር ፍትሕ ላይ ያተኮሩ ተከታታይ የአሰልጣኞች ስልጠናዎችን በተለያዩ ከተሞች ሰጥቷል።

የአረጋውያን ሰብአዊ መብቶች እንዲሁም መብቶቹን ለማስከበርና ለማስፋፋት የሚያስችሉ ክህሎቶችን በተመለከተ ከየካቲት 2 እስከ 6 ቀን 2018 ዓ.ም. ከሲዳማ እና ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ለተውጣጡ የአረጋውያን እና የጡረተኞች ማኅበራት አመራሮችና አባላት በሃዋሳ እና በአርባ ምንጭ ከተሞች፤ ከመጋቢት 14 እስከ 17 ቀን 2018 ዓ.ም. ለትግራይ አረጋውያን ማኅበር አባላት በመቀሌ ከተማ፤ እንዲሁም ከመጋቢት 21 እስከ 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ለሐረሪ ክልል አረጋውያን እና ጡረተኞች ማኅበራት አባላት በሐረር ከተማ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል። ስልጠናዎቹ የስልጠናው ተሳታፊዎች አረጋውያን ላይ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን ሪፖርት እና ውትወታ የማድረግ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ የሚያስችሉ ተግባራዊ ልምምዶችን ያካተቱ ናቸው።

በተጨማሪም ኢሰመኮ በሕፃናት መብቶች ጥበቃ ዙሪያ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አባላት እና የሥራ ኃላፊዎች ከየካቲት 10 እስከ 13 ቀን 2018 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል። ይህ ስልጠና ሕፃናት በወንጀል ድርጊት ተሳታፊ ወይም ተጎጂ በሚሆኑበት ጊዜ ሊከበሩላቸው የሚገቡ መብቶችን በተመለከተ በስልጠናው የተሳተፉ አካላትን ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ ሲሆን፣ ተሳታፊዎች በቡድን ውይይት አማካኝነት ልምድ ተለዋውጠዋል። በሌላ በኩል፣ ከባሌ ዞን እና ከሮቤ ከተማ የሴቶች እና የሕፃናት ጽሕፈት ቤቶች ለተውጣጡ ባለሙያዎች ከየካቲት 30 እስከ መጋቢት 4 ቀን 2018 ዓ.ም. የሴቶች መብቶች ላይ ያተኮረ ስልጠና በሮቤ ከተማ ተሰጥቷል።

የታራሚዎችን አያያዝ በተመለከተ፣ ከማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ ማረሚያ ቤቶች እና ከፍትሕ ቢሮ ለተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች ከየካቲት 9 እስከ 13 ቀን 2018 ዓ.ም. በሆሳዕና ከተማ፤ እንዲሁም ከአማራ ክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን እና ከስድስት ማረሚያ ቤቶች ለተውጣጡ የማረሚያ ቤት ፖሊስ አባላት ከመጋቢት 21 እስከ 25 ቀን 2018 ዓ.ም. በባሕር ዳር እና ኮምቦልቻ ከተሞች ስልጠና ተሰጥቷል። በተጨማሪም የፖሊስ አባላት ሰብአዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር ዐቅም ለመገንባት ያለመ ስልጠና በወንጀል መከላከልና ምርመራ ዘርፍ ለተሰማሩ የፖሊስ አባላት ከየካቲት 9 እስከ 13 ቀን 2018 ዓ.ም. በሆሳዕና ከተማ፤ ከየካቲት 16 እስከ 20 ቀን 2018 ዓ.ም. በደሴ ከተማ እና ከመጋቢት 14 እስከ 17 ቀን 2018 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል። ስልጠናዎቹ የታራሚዎች እና ተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝን በተመለከተ ዕውቀት፣ አመለካከት እና ክህሎትን ለመገንባት የሚያግዙ ናቸው።

በሌላ በኩል ኢሰመኮ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች ዙሪያ ከሐረሪ እና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተውጣጡ ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች አገልግሎት ለሚሰጡ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ከየካቲት 30 እስከ መጋቢት 4 ቀን 2018 ዓ.ም. በሐረር እና በአሶሳ ከተሞች ስልጠና ሰጥቷል፡፡ የስልጠናው ተሳታፊዎችም በስልጠናው ያገኙትን የሰብአዊ መብቶች ዕውቀት፣ እና ክህሎት በመጠቀም ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ ያላቸውን ተነሳሽነት ገልጸዋል፡፡  

በሌላ በኩል ኢሰመኮ ከፕሮጀክት ኤክስፒዳይት ጀስቲስ (Project Expedite Justice) ጋር በመተባበር የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶች በሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ ያላቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻልና የሽግግር ፍትሕ ሂደትን ለማጠናከር ከአማራ ክልል ለተውጣጡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከጥር 4 እስከ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል። በተመሳሳይ የኪነ ጥበብ እና ሥነ ጥበብ ባለሙያዎች በሽግግር ፍትሕ ትግበራ ወቅት ያላቸውን ሚና በተመለከተ ከድሬዳዋ እና ከሐረር ለተውጣጡ ባለሙያዎች ከጥር 26 እስከ 30 ቀን 2018 ዓ.ም. በድሬዳዋ፣ እንዲሁም ከጅማ እና ከአጋሮ ለተውጣጡ ባለሙያዎች ከየካቲት 16 እስከ 20 ቀን 2018 ዓ.ም. ስልጠናዎች ተሰጥተዋል።

በተጨማሪም በሰብአዊ መብቶች እና በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ የወጣቶችን ሚና ለማሳደግ ቀደም ሲል የአሰልጣኞች ስልጠና የወሰዱ የሶዶ ከተማ የወጣቶች ማኅበራት አመራሮች፣ ከጥር 28 እስከ 30 ቀን 2018 ዓ.ም. ለ40 አባላቶቻቸው በሶዶ ከተማ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡ ኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች እሴቶች እና መርሖች እንዲሁም ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ የአካል ጉዳተኞች መብቶችን በተመለከተ ከመጋቢት 22 እስከ 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ለአካል ጉዳተኞች ማኅበራት አመራሮች እና አባላት በጋምቤላ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል።