Skip to content
Facebook XYouTube Linkedin Flicker TikTok Instagram WhatsApp Telegram
Ethiopian Human Rights Commission – EHRC
  • About
    • Who We Are
    • Our Team
    • Careers
    • Contact Us
  • Regions
        • Regions

          EHRC is an independent federal institution tasked with the promotion and protection of human rights in Ethiopia.

        • Addis Ababa
        • Afar
        • Amhara
        • Benishangul Gumuz
        • Gambella
        • Oromia
        • Somali
        • Tigray
        • Central Ethiopia
        • Dire Dawa
        • Harari
        • Sidama
        • South Ethiopia
        • South West Ethiopia Peoples'
  • Areas of Work
        • Areas of Work

          We are an independent national human rights institution tasked with the promotion & protection of human rights in Ethiopia.

        • Economic, Social & Cultural Rights
        • Civil & Political Rights
        • IDPs, Refugees & Migrants’ Rights
        • Rights of Persons with Disabilities & the Rights of Older Persons
        • Women’s & Children’s Rights
        • Human Rights Education
        • Human Rights Monitoring & Investigation
        • Human Rights Film Festival
        • Human Rights Moot Court Competition
  • Press Releases
  • Reports
  • Media
    • EHRC on the News
    • EHRC Newsletters
    • EHRC Videos
    • EHRC Visuals
  • Latest
    • Expert Views
    • Explainers
    • Event Updates
    • Annual Ethiopia Human Rights Situation Reports
  • Resources
 
Ethiopian Human Rights Commission – EHRCEthiopian Human Rights Commission – EHRC

ንግድና ሰብአዊ መብቶች

September 29, 2023September 29, 2023 Explainer

የንግድ ተግባራት በአግባቡ ካልተመሩ የጤና፣ የመኖሪያ ቤት፣ የምግብ፣ ውሃ፣ ማኅበራዊ ደኅንነት፣ የመሥራት መብት፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ የሥራ ሁኔታ የማግኘት እንዲሁም የንግድ ማኅበራትን የመመሥረትና የመቀላቀል መብቶች አተገባበር ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራሉ

Twitter Facebook Telegram Email Whatsapp Print

የንግድ ተግባራት እና ሰብአዊ መበቶች ምን ትስስር አላቸው?

የንግድ ተግባራት ሰብአዊ መብቶች ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ:: ብዙ ጊዜ እነዚህ ተጽዕኖዎች ባለብዙ ገጽታ እና እንደሁኔታው የሚለያዩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የንግድ ተግባራት ተጨማሪ የሥራ ወይም የልማት ዕድሎችን በመፍጠር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሥራ መብት እስከ ምግብ እና መጠለያ እንዲሁም ጤና እና ትምህርት መብቶች የሚሟሉባቸውን መንግዶች በማመቻቸት በተለይም በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች መተግበር ላይ ጠቃሚ እና አውንታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ፡፡ የንግድ ተግባራት በአግባቡ ካልተመሩ የኢኮኖሚያዊ፣ የማኅበራዊ እና ባህላዊ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን ላይ የተቀመጡ የጤና፣ የመኖሪያ ቤት፣ የምግብ፣ ውሃ፣ ማኅበራዊ ደኅንነት፣ የመሥራት መብት፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ የሥራ ሁኔታ የማግኘት እንዲሁም የንግድ ማኅበራትን የመመሥረትና የመቀላቀል መብቶች አተገባበር ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራሉ። ለምሳሌ አደገኛ የሆኑ የንግድ ሥራዎችን (እንደ ማዕድን ማውጣት) ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች በሆኑ ሰዎች መከወን፣ ከንግድ ሥራዎች በሚፈጠር ብክለት (እንደ መርዛማ ኬሚካሎች) በሠራተኞች እና/ወይም በዙሪያው ያሉ ኅብረተሰቦች ጤንነት፣ መተዳደሪያ/ኑሮ ብሎም የመኖር መብት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን መፍጠር እንዲሁም ለጤና አደገኛ የሆኑ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ የተጠቃሚዎችን ወይም ደንበኞችን ጤና አደጋ ላይ መጣል ይችላሉ፡፡ ይህም የንግድ ተግባራት እና የሰብአዊ መብቶች ርዕሰ ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ እ.ኤ.አ በ2011 የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት፣ የተባበሩት መንግሥታት የንግድ እና ሰብአዊ መብቶች መመሪያ መርሖችን/United Nations Guiding Principles on Business and Human Rights (UNGPs)/አጽድቋል።

የተባበሩት መንግሥታት የንግድ እና ሰብአዊ መብቶች መመሪያ መርሖች ምንድናቸው? 

የተባበሩት መንግሥታት ንግድ እና ሰብአዊ መብቶች መመሪያ መርሖች፣ ከንግድ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከልና ለማስወገድ የሚረዳ የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ መስፈርት ያቀረቡ እና ከንግድ ተግባራት ጋር በተያያዘ የመንግሥታት እና የንግድ ድርጅቶች ግዴታዎችን እና ኃላፊነቶችን የሚያስረዱ ናቸው። በመመሪያ መርሖች መሠረት መንግሥታት እና የንግድ ተቋማት የተለዩ ግን የተሳሰሩ ኃላፊነቶች እና ግዴታዎች አሏቸው። የመመሪያ መርሖቹ፤ በሁሉም ሀገራት እንዲሁም መጠናቸው፣ ዘርፋቸው፣ የሚገኙበት ቦታ፣ የባለቤትነት ሁኔታቸው እና መዋቅራችው ሳይወስናቸው እና ልዩነት ሳይደረግባቸው በሁሉም የንግድ ተቋማት ላይ ተፈጻሚ የሚሆኑ ናችው፡፡

የንግድ እና ሰብአዊ መብቶች መመሪያ መርሖች፤ ዓምዶችና ይዘቶች ምን ይመስላሉ? 

ንግድ እና ሰብአዊ መብቶች መመሪያ የመንግሥታትን መብቶችን የመጠበቅ ግዴታ/duty to protect/፣ የንግድ ድርጅቶችን ሰብአዊ መብቶችን የማክበር ኃላፊነት/respect/ እና ከንግድ ጋር የተያያዙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ የማስተካከል ወይም መፍትሔ የመስጠት/access to remedies/ ኃላፊነትን በሚያስረዱ ሦስት ዓምዶች/pillars/ እና የንግድ ተግባራትን በተመለከት የሰብአዊ መብቶችን ጥበቃ ለማረጋገጥ በሚረዱ 31 መርሖች የተደራጀ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ዓምድ ሥር በንግድ አውድ ውስጥ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መሠረታዊ እና የአሠራር መርሖች ተካተዋል፡፡

መጠበቅ (ዓምድ 1) 

ይህ ዓምድ 10 መርሖች (መርሕ 1 – 10) የያዘ ሲሆን በንግድ ሥራ አውድ ውስጥ የመንግሥታትን ሰብአዊ መብቶችን የመጠበቅ ግዴታ የሚገልጽ ነው። በመርሕ 1 እንደተቀመጠው ሀገራት በግዛታቸው ውስጥ የንግድ ተቋማትን ጨምሮ በሦስተኛ ወገኖች ሰብአዊ መብቶች እንዳይጣሱ ጥበቃ የማድረግ ግዴታ አለባቸው። ይህም ውጤታማ ፖሊሲዎችን፣ ሕጎችን፣ ደንቦችን እና የፍትሕ ሥርዓትን ሥራ ላይ በማዋል ጥሰቶችን ለመከላከል፣ ለመመርመር እና ተጠያቂነትን ለማስፈን ተገቢውን እርምጃ መውሰድን ይጠይቃል። ከዚህም በተጨማሪ ሀገራት በግዛታቸው ውስጥ ወይም በሥልጣናቸው ሥር የሚገኙ የንግድ ድርጅቶች በሙሉ ተግባራቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ሰብአዊ መብቶችን ማክበር እንደሚጠበቅባቸው በግልጽ ማስቀመጥ አለባቸው። ምንም እንኳን መንግሥታት በግል ተዋናዮች ለሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በቀጥታ ተጠያቂ ባይሆኑም በግል ተዋናዮች የሚደርሱ ጥሰቶችን ለመከላከል፣ ለመመርመር፣ ተጠያቂ ለማድረግ እና ለማረም ተገቢውን እርምጃ ባለመውሰድ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች የተጣሉባችውን ግዴታዎቻቸውን ሊጥሱ ይችላሉ፡፡

የንግድ እና ሰብአዊ መብቶች መመሪያ መርሖች፣ የአሠራር መርሖችን /operational principles/ ያካተቱ ሲሆን ሀገራት የመጠበቅ ግዴታቸውን ሲወጡ ሊወስዷቸው የሚገቡ እርምጃዎችም ተዘርዝረዋል። ከእነዚህም ውስጥ የንግድ ኢንተርፕራይዞች ሰብአዊ መብቶችን እንዲያከብሩ የሚጠይቁ ሕጎችን ሥራ ላይ ማዋል እና በየጊዜው የሕጎቹን በቂነት መገምገም፣ ክፍተቶችን ማረም እና የንግድ ተቋማት የሰብአዊ መብቶችን አክብረው እንዲሠሩ የሚያስችላቸውን ውጤታማ መመሪያ መስጠት ይገኙባቸዋል። በተጨማሪም መርሖቹ በመንግሥታት ባለቤትነት ወይም ቁጥጥር ሥር ያሉ እንዲሁም ከመንግሥት ከፍተኛ ድጋፍ እና አገልግሎቶችን በሚቀበሉ የንግድ ድርጅቶች ሊደርሱ የሚችሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመከላከል ተጨማሪ እርምጃዎችን ሊወስዱ እንደሚገባ ያስገነዝባል፡፡ በሌላ በኩል መንግሥታት በሰብአዊ መብቶች መረጋገጥ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ከንግድ ኢንተርፕራይዞች ጋር ውል ሲገቡ ወይም ይህንን የተመለከተ ሕግ ሲያወጡ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ግዴታቸውን ለመወጣት የሚያስችል በቂ ቁጥጥር ማድረግ እንዳለባቸው ተመላክቷል። ይህም መንግሥታት በሰብአዊ መብቶች ተጠቃሚነት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ አገልግሎቶችን ወደ ግል ሲያዘዋውሩ (privatization) በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች የተጣለባቸው ግዴታ ቀሪ እንደማይሆን ያሳያል።

ማክበር (ዓምድ 2)  

ይህ ዓምድ 14 መርሖች (መርሕ 11 – 24) የያዘ እና የንግድ ድርጅቶች ያለባቸውን ሰብአዊ መብቶችን የማክብር ኃላፊነት የሚገልጽ ነው። የንግድ ተቋማት ሰብአዊ መብቶችን የማክበር ኃላፊነት፤ የሌሎችን ሰብአዊ መብቶች ከመጣስ መቆጠብን እና የተሳተፉባቸውን ወይም አስተዋጽዖ ያደረጉባቸውን አሉታዊ የሰብአዊ መብቶች ተጽዕኖዎች መፍታትን ያካትታል፡፡ በመርሕ 12 እንደተቀመጠው የንግድ ተቋማት ሰብአዊ መብቶችን የማክበር ኃላፊነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥበቃ የሚደረግላቸውን ሰብአዊ መብቶች የሚያመላክት ነው።

የንግድ ተቋማት ሰብአዊ መብቶችን የማክበር ኃላፊነት፣ መጠናቸው እና ዘርፋቸው፣ የሥራ ሁኔታ፣ የባለቤትነት እና የአወቃቀር ሁኔታቸው ምንም ይሁን ምን በሁሉም ኢንተርፕራይዞች ላይ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን ኃላፊነታቸውን የሚወጡባቸው መንገዶች መጠን እና ውስብስብነት ግን በእነዚህ በተጠቀሱት ሁኔታዎች እና ተቋማቱ መብቶች ላይ ሊያደርሱ እንደሚችሉት ተጽዕኖ ክብደት ሊለያዩ እንደሚችሉ በመርሕ 14 ተገልጿል።

ከላይ ከተገለጹት በተጨማሪ መርሖቹ የንግድ ተቋማት እንደ መጠናቸው እና ሁኔታቸው ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ተስማሚ የሆኑ ፖሊሲዎች እና ሂደቶችን መቅረጽ፤ በራሳቸው እንቅስቃሴዎች ወይም በንግድ ግንኙነታቸው ምክንያት የሚደርሱ ወይም ሊደርሱ የሚችሉ አሉታዊ የሰብአዊ መብቶች ተጽዕኖዎችን መገምገም እና መለየት፤ አሉታዊ የሰብአዊ መብቶች ተጽዕኖዎችን ለመከላከል እና ለማቃለል የተጽዕኖ ግምገማ ግኝቶቹን መሠረት በማድረግ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንዲሁም የወሰዷቸውን እርምጃዎች ውጤታማነት መከታተል ያለባቸው መሆኑን ይዘረዝራሉ። በመርሖቹ ከላይ የተዘረዘሩትን ጨምሮ ሌሎች የንግድ ድርጅቶች የሚያደርሱትን አሉታዊ የሰብአዊ መብቶች ተጽዕኖ እንዲለዩ እና እነሱን ለመፍታት እንዲችሉ የሚረዱ አካሄዶችም ተዘርዝረዋል።

መፍትሔ መስጠት (ዓምድ 3) 

ይህ ዓመድ 7 መርሖች (መርሕ 25-31) የያዘ ሲሆን ለጥሰቶች መፍትሔ በመስጠት ላይ ያተኮረ ነው። ሰዎችን ከንግድ ነክ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መጠበቅ የመንግሥታት ግዴታ አካል እንደመሆኑ መጠን፤ በግዛታቸው ውስጥ እና/ወይም በሥልጣናቸው ሥር እንደዚህ ዐይነት በደል ሲደርስ በፍርድ ቤት የሚሰጥ /judicial/፣ በአስተዳደር፣ ሕግ በማውጣት ወይም በሌሎች ተገቢ መንገዶች ተጎጂዎች ውጤታማ መፍትሔ የሚያገኙበትን መንገድ ለማረጋገጥ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እዳለባቸው በመርሕ 25 ተገልጿል። ከንግድ ጋር የተገናኙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ሲፈጸሙ መንግሥታት ለመመርመር፣ ለመቅጣት እና ለማስተካከል ተገቢውን እርምጃ ካልወሰዱ፤ የመንግሥትን የመጠበቅ ግዴታ ደካማ ወይም ትርጉም የለሽ ሊያደርገው ይችላል።

ውጤታማ መፍትሔ /effective remedy/ ማግኘት ሥነ-ሥርዓታዊ/procedural/ እና መሠረታዊ/substantive/ ገጽታዎች አሉት። የመፍትሔ ሥነ-ሥርዓቶች ገለልተኛ፣ ከሙስና የተጠበቁ እንዲሁም በውጤቱ ላይ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ፖለቲካዊ ወይም ሌሎች ሙከራዎች የጸዱ መሆን አለባቸው። የቅሬታ ማቅረቢያ ዘዴዎችን በመጠቀም ለሚቀርቡ አቤቱታዎች የሚሰጡ መፍትሔዎች የተለያዩ ተጨባጭ ቅርጾችን ሊወስዱ የሚችሉ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ዓላማቸው ሲታይ፣ ለተከሰቱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምላሽ መስጠት ወይም የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ነው። ይቅርታ፣ ካሳ፣ የወንጀልም ሆነ አስተዳደራዊ ቅጣቶች፣ እንዲሁም ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል የሚረዱ እገዳዎች ወይም ጥሰትን ያለመድገም ዋስትናዎች እዚህ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ፡፡

በመመሪያ መርሖች መሠረት የቅሬታ ማቅረቢያ ዘዴ፣ ከንግድ ነክ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ጋር በተያያዘ ቅሬታ የሚነሳበት እና መፍትሔ የሚፈለግበትን ማንኛውንም መደበኛ፣ መንግሥታዊ /state based/ ወይም መንግሥታዊ ያልሆነ/non-state/፣ በፍርድ ቤት /judicial/ ወይም ከፍርድ ቤት ውጪ /non-judicial/ የሚሰጥ የመፍትሔ ሂደቶችን የሚያመላክት ነው።

  • በፍርድ ቤት የሚሰጥ የመንግሥት የመፍትሔ ስልቶች /state based judicial mechanisms/ 

ውጤታማ የፍትሕ ሥርዓት ለጥሰቶች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት እጅግ አስፈላጊ እና ዋናው ነው። የፍትሕ አካላቱ ከንግድ ጋር የተያያዙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የመፍታት ዐቅማቸው በገለልተኝነት፣ ታማኝነት እና ተገቢውን ሥነ-ሥርዓት/procedure/ የመከተል ችሎታቸው ላይ የተመሠረተ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ መርሕ 26፣ ሀገራት በሀገር ውስጥ ፍርድ ቤት የሚሰጥ የመፍትሔ ስልቶች ውጤታማነት ለማረጋገጥ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው እና ይህም መፍትሔ ከማግኘት መከልከልን የሚያስከትሉ የሕግ፣ የተግባር/practical/ እና ሌሎች ተዛማጅ መሰናክሎችን የሚቀንሱበትን መንገድ ግምት ውስጥ ማስገባትን እንደሚያጠቃልል ያስቀምጣል።

  • ከፍርድ ቤት ውጪ የሚሰጥ የመንግሥት የመፍትሔ ስልቶች/state based non-judicial mechanisms/ 

የፍትሕ ሥርዓቶች ውጤታማ እና በቂ ሀብት ቢኖራቸውም ሁሉንም የመብቶች ጥሰቶችን መፍታት አይችሉም። በተጨማሪም ሁልጊዜ ተፈላጊ እና በሁሉም ቅሬታ አቅራቢዎች ተመራጭ አካሄድ ላይሆኑ ይችላሉ።

አስተዳደራዊ፣ ሕግ የማውጣት እና ሌሎች ከፍርድ ቤት ውጪ የሆኑ የመፍትሔ ስልቶች በፍርድ ቤት የሚሰጡ የመፍትሔ አካሄዶችን በመደገፍ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘ መርሕ 26 ንግድ ነክ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመፍታት መንግሥታት ከፍርድ ቤት መፍትሔ ስልቶች ጋር ጎንለጎን መንግሥት ላይ የተመሠረቱ ከፍርድ ቤት ውጪ የሆኑ ውጤታማ የቅሬታ ዘዴዎችን ማቅረብ እንዳለባቸው ያስቀምጣል። ሀገራት እነዚህን ዘዴዎች ሲተገብሩ፣ እንደ ፍርድ ቤት መፍትሔ አሠራሮች ሁሉ፣ ከንግድ ነክ የሰብአዊ መብቶች ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ በቅሬታ አቅራቢ እና ቅሬታ በቀረበበት አካል መካከል የሚፈጠሩ ማናቸውንም የኃይል አለመመጣጠን፣ የተጋላጭነት ወይም የመገለል ሥጋትን የመሳሰሉ እንቅፋቶችን ለመፍታት መንገዶችን ማጤንም ይኖርባቸዋል።

አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ከፍርድ ቤት ውጪ ስልቶችን በማስፋፋት እና/ወይም አዳዲስ አሠራሮችን በመጨመር ከንግድ ጋር በተያያዙ የሰብአዊ መብቶች ጥስቶች መፍትሔ አሰጣጥ ላይ ያሉ ክፍተቶችን መሙላት ይቻላል። እነዚህም ከመብቶች ጋር የሚጣጣሙ /የሰብአዊ መብቶች ተኮር አወቃቀር/ ሂደቶችን የሚከተሉ ማስማማት/mediation/ ላይ የተመሠረቱ ወይም ሌሎች ተገቢ እና ባህላዊ ሂደቶችን የሚከተሉ ሊሆኑ ይችላሉ።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢኮኖሚያዊ፣ የማኅበራዊ እና ባህላዊ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን ኮሚቴ በአጠቃላይ ትንታኔ ቁጥር. 24 እንደገለጸው ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ከንግድና ሰብአዊ መብቶች ጋር ተያይዞ መንግሥት የተጣለበትን ግዴታ እየተወጣ ስለመሆኑ ክትትል ማድረግ እና ከተጎጂዎች አቤቱታ መቀበል የሚያስችል አደረጃጀት እንዲኖራቸው እና ሊበረታቱ እንደሚገባ አጽኖት ሰጥቶበታል።

  • በመንግሥት ላይ ያልተመሠረቱ እና ከፍርድ ቤት ውጪ የሆኑ ስልቶች/non state non-judicial mechanisms/ 

የተባበሩት መንግሥታት የንግድ እና ሰብአዊ መብቶች መመሪያ መርሖች፣ መርሕ 27 ሀገራት ንግድ ነክ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በተመለከተ መንግሥታዊ ያልሆኑ የቅሬታ ማቅረቢያ ዘዴዎችን ማግኘት የሚቻልበትን መንገድ ማመቻቸት እንዳለባቸው ያስገነዝባል። መንግሥታዊ ያልሆኑ የቅሬታ ዘዴዎች በአንድ የንግድ ድርጅት ብቻ ወይም ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ፣ በኢንዱስትሪ ማኅበር ወይም በብዙ ባለድርሻ አካላት የሚተዳደሩትን ዘዴዎቸን የሚያጠቃልሉ ሲሆን ምንም እንኳ የዳኝነት አካላት ባይሆኑም ውሳኔ የመስጠት/adjudication/፣ በውይይት ላይ የተመሠረተ ወይም ሌላ ባህላዊ እና ከመብቶች ጋር የሚጣጣሙ ሂደቶችን ሊጠቀሙ ይችላሉ። በሌላ በኩል አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች አካላትም በዚህ ምድብ ይጠቃለላሉ።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ቅሬታዎች ቶሎ እንዲፈቱ እና በቀጥታ እንዲታረሙ ለማድረግ የንግድ ተቋማት በሥራ ቦታ /operational level/ የቅሬታ ዘዴዎችን ማዘጋጀት እንዳለባቸው መርሕ 29 ያስቀምጣል። እነዚህ ዘዴዎች በንግድ ድርጅቶች አሉታዊ ተጽዕኖ ለሚደርስባቸው ግለሰቦች እና ማኀበረሰቦች በቀጥታ ተደራሽ ከመሆናቸው ባለፈ ቅሬታዎች ከተለዩ በኋላ በንግድ ድርጅቱ በፍጥነት እና በቀጥታ እንዲታረሙ በማድረግ ጉዳቱ እንዳይባባስ እና ቅሬታዎች እንዳይጨምሩ ያደርጋሉ። ድርጅቶች የቅሬታ ይዘቶችን በመከተል እና በመተንተን አሉታዊ የሰብአዊ መብቶች ተጽዕኖዎችን በመለየት ቀጣይነት ያለው ተገቢ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እና አሠራሮቻቸውን በዚሁ መሠረት ማስተካከል እንዲችሉም ያግዛሉ።

በመርሖቹ ከፍርድ ቤት ውጪ ለሆኑ /non judicial/ የቅሬታ ማቅረቢያ ዘዴዎች የውጤታማነት መስፈርቶች ተዘርዝረዋል። በዚህም መሠረት በመንግሥት ላይ የተመሠረቱ እና በመንግሥት ላይ ያልተመሠረቱ ከፍርድ ቤት ውጪ የሆኑ የቅሬታ ማቅረቢያ ዘዴዎች ቅቡል/legitimate/፣ ተደራሽ/accessible/፣ ፍትሐዊ፣ ተገማች/predictable/፣ ግልጽ፣ ከሰብአዊ መብቶች ጋር ሚጣጣሙ፣ ቀጣይነት ያለው የትምህርት ምንጭ መሆን ያለባቸው ሲሆን፣ በንግድ ተቋማት የተዘጋጁ የቅሬታ ማቅረቢያ ዘዴዎች/operational level/ ደግሞ በተጨማሪነት አሳታፊ እና በንግግር/በውይይት/ ላይ የተመሠረቱ ሊሆኑ ይገባል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ከነሐሴ 30 እስከ ጳጉሜን 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ አህጉራዊ የአፍሪካ የንግድ ሥራ እና ሰብአዊ መብቶች መድረክን አስተናግዳለች። የተባበሩት መንግሥታት የንግድ እና ሰብአዊ መብቶች መመሪያ መርሖች መጽደቅን ተከትሎ ሀገራትና አህጉራዊ ተቋማት በንግድና በሰብአዊ መብቶች ላይ የድረጊት መርኃ ግብር አዘጋጅተዋል። ኢትዮጵያ የንግድ ሥራ እና ሰብአዊ መብቶችን በተመለከተ እምበዛም ሥራዎችን ካልሠሩ ሀገራት ተርታ ተመድባለች። ይህም ሀገሪቱ የንግድ ሥራ እና ሰብአዊ መብቶች ድርጊት መርኃ ግብርን ከማዘጋጀት ጀምሮ ሌሎች እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለባት አመልካች ነው።

Related posts

October 23, 2023October 27, 2023 Event Update
በብሔራዊ የንግድ እና ሰብአዊ መብቶች የድርጊት መርኃ ግብር ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተካሄደ ውይይት
May 23, 2023August 28, 2023 EHRC Quote
በአዲስ አበባ ከተማ የንግድ ቤቶችን ከማፍረስ ሂደት ጋር በተያያዘ አካል ጉዳተኞች ለኢሰመኮ ያቀረቡትን አቤቱታ በተመለከተ
November 29, 2022November 30, 2022 Human Rights Concept
ቴክኖሎጂ እና የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ
June 18, 2021February 12, 2023 Press Release
በምርጫው ወቅት የሕግ አስከባሪ አካላት ሰብአዊ መብቶችን አክብረው መንቀሳቀስ አለበቸው

Signup for the Latest Update from EHRC

Submit your email to singup
Facebook Like us on FacebookXFollow us on XYouTube Follow us on YouTubeLinkedin Follow us on LinkedinWhatsApp WhatsAppTikTok TikTokTelegram TelegramInstagram InstagramFlicker Flickr

Useful Links

  • NANHRI
  • GANHRI
  • OHCHR
  • ACHPR
  • TRANSITIONAL JUSTICE

Get Involved

  • Jobs
  • Events
  • Contact Us
  • Telegram Bot
  • Subscribe to our newsletter

Connect with Us

  • Facebook
  • Twitter
  • LinkedIn
  • YouTube
  • Flickr
  • Instagram
Descriptive Text

We are an independent
national human rights
institution tasked with
the promotion and protection of human
rights in Ethiopia.

Submit your email to get the latest update from EHRC

Address: Sunshine Tower No. 5, Meskel Square, on Bole Road next to Hyatt Regency Hotel, Addis Ababa, Ethiopia
Tel: +251115504031 | Fax: +251 11 550 4125 | PO Box 1165 Addis Ababa | Email: info@ehrc.org


The contents of this website, excepting third party content for which the Commission bears no responsibility,
may be freely used and copied for educational and other non-commercial purposes, provided that any such reproduction is accompanied by an acknowledgement of the Ethiopian Human Rights Commission (EHRC). Source of images used in the content of this website: EHRC Media and Communications Department Archive and Creative Common License.

This website is managed by the Media and Communications team of the Ethiopian Human Rights Commission (EHRC).

We are using cookies to give you the best experience on our website.

You can find out more about which cookies we are using or switch them off in .

Scroll to top
  • About
    • Who We Are
    • Our Team
    • Careers
    • Contact Us
  • Regions
    • Addis Ababa
    • Afar
    • Amhara
    • Benishangul Gumuz
    • Central Ethiopia
    • Dire Dawa
    • Gambella
    • Harari
    • Oromia
    • Sidama
    • Somali
    • South Ethiopia
    • South West Ethiopia Peoples’
    • Tigray
  • Areas of Work
    • Economic, Social & Cultural Rights
    • Civil & Political Rights
    • IDPs, Refugees & Migrants’ Rights
    • Rights of Persons with Disabilities & the Rights of Older Persons
    • Human Rights Monitoring & Investigation
    • Women’s & Children’s Rights
    • Human Rights Education
    • Human Rights Film Festival
    • Human Rights Moot Court Competition
  • Press Releases
  • Reports
  • Media
    • EHRC on the News
    • EHRC Newsletters
    • EHRC Videos
    • EHRC Visuals
  • Latest
    • Expert Views
    • Explainers
    • Event Updates
    • Annual Ethiopia Human Rights Situation Reports
  • Resources
Facebook XYouTube Linkedin Flicker TikTok Instagram WhatsApp Telegram
Search
Ethiopian Human Rights Commission - EHRC
Powered by  GDPR Cookie Compliance
Privacy Overview

This website uses cookies so that we can provide you with the best user experience possible. Cookie information is stored in your browser and performs functions such as recognising you when you return to our website and helping our team to understand which sections of the website you find most interesting and useful.

Strictly Necessary Cookies

Strictly Necessary Cookie should be enabled at all times so that we can save your preferences for cookie settings.

If you disable this cookie, we will not be able to save your preferences. This means that every time you visit this website you will need to enable or disable cookies again.