የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እ.ኤ.አ. በየዓመቱ ሰኔ 8 ቀን ታስቦ የሚውለውን ዓለም አቀፉን የአረጋውያን ጥቃት ግንዛቤ ማስጨበጫ ቀን አስመልክቶ ሰኔ 11 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የውይይት መድረክ አካሂዷል። ውይይቱ ከኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበር፣ ከሄልፕ ኤጅ ኢትዮጵያ (HelpAge Ethiopia) እና ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን፤ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአረጋውያን ማኅበራት ተወካዮች እና የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ተሳትፈዋል።

በመድረኩ ኢሰመኮ የአረጋውያንን መብቶች በማስከበር ረገድ የሚያከናውናቸውን የሰብአዊ መብቶች ክትትል፣ የትምህርትና ሥልጠና እንዲሁም የዐቅም ማጎልበቻ ተግባራትን የተመለከተ ማብራሪያ ቀርቧል። በተጨማሪም አረጋውያን በዕለት ከዕለት ሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ለምሳሌ የጤና እና የሕዝብ ትራንስፖርትን ጨምሮ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚደርስባቸው እንግልት እንዲሁም የጡረታ ገቢያቸው በሀገሪቱ ካለው የኑሮ ውድነት እና ተጨባጭ የኢኮኖሚ ሁኔታ አንጻር ዝቅተኛ መሆን፣ ይህም አረጋውያንን ጥገኞች እንዲሆኑ በማድረግ ለልዩ ልዩ ኢኮኖሚያዊ ጥቃቶች ይበልጥ ተጋላጭ የሚያደርግ ሁኔታ መፍጠሩን በመድረኩ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በአረጋውያን ላይ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን ለመከላከልና ለማስቀረት በየደረጃው ያሉ የአረጋውያን ማኅበራትን ማጠናከር፣ ሁሉም የመንግሥት ተቋማትና አገልግሎት ሰጪዎች የአረጋውያን ፍላጎቶችን መሠረት ያደረጉ ተግባራትን የአካቶ ሥልት መንደፍ፣ የአረጋውያንን የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳቶች ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚያግዙ ተጨማሪ የእንክብካቤ እና የድጋፍ ሥርዓቶች መዘርጋት፣ እንዲሁም የአረጋውያን መብቶችን ያገናዘቡ የሕግና ፖሊሲ ማእቀፎችን ማውጣትና ትግበራቸውን መከታተል፣ የጥቃት ማሳወቂያና ምላሽ መስጫ መንገዶችን ማስፋፋት እና በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰድ በመንግሥት ሊወሰዱ የሚገቡ ወሳኝ እርምጃዎች መሆናቸው በውይይቱ ተመላክቷል።

የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር መሐመድ አሕመድ፡- አረጋውያን ለዘርፈ ብዙ ጥቃቶች ያላቸውን ተጋላጭነት አስታውሰው፣ በአረጋውያን ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለማስቀረት ግንዛቤ ከማስፋፋት ሥራዎች ጎን ለጎን ተግባራዊ ምላሽ የሚሰጥ የሕግ፣ የፖሊሲና ተቋማዊ ማእቀፍ መዘርጋት እንደሚገባ ገልጸዋል። አክለውም አረጋውያን ሀገሪቱ በሚከናወን ልማት ከሌሎች ሰዎች እኩል ተጠቃሚ የመሆን መብት ያላቸው በመሆኑ መንግሥት የአረጋውያንን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ እርምጃዎችን የመውሰድ ኃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል።