የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ በዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ የተመራ ልዑካን ቡድን፤ ከመጋቢት 21 እስከ 23 ቀን 2018 ዓ.ም. በጄኔቫ፣ ስዊዘርላንድ በተካሄደው የብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት ዓለም አቀፍ ጥምረት (GANHRI) ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ተሳትፏል። ለሦስት ቀናት የተካሄደው ይህ መድረክ የጥምረቱ ቢሮ ስብሰባን፣ ጠቅላላ ጉባኤን፣ የቀጠናዊ ትስስር ስብሰባዎችን፣ የዕውቀት ልውውጥ መድረኮችን እና የጥምረቱን ዓመታዊ ኮንፍረንስ ያካተተ ነበር።

መጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም. ዋና ኮሚሽነሩ በአሁኑ ወቅት በምክትል ሰብሳቢነት በሚመሩት የአፍሪካ ብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት ትስስር (NANHRI) ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል። በማግስቱ ደግሞ በብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት ዓለም አቀፍ ጥምረት (GANHRI) ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በመገኘት ስለ ጥምረቱ የሥራ እንቅስቃሴዎች፣ ስለ ብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት የዕውቅና አሰጣጥ (Accreditation) ሂደት ወቅታዊ መረጃዎች ልውውጥ፣ እንዲሁም የኅብረቱን ቀጣይ የሥራ ዕቅድ እና በጀት በማጽደቅ ሂደቶች ላይ ተሳትፎ አድርገዋል።

ከጠቅላላ ጉባኤው በመቀጠል “በእንቅስቃሴ ላይ ላሉ ሰዎች ጥበቃ እና ማካተት፦ ገለልተኛ ክትትል፣ ተጠያቂነት እና መብቶችን ማግኘት” በሚል መሪ ቃል የልምድ ልውውጥ ተካሂዷል። በመድረኩ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት በስደት ላይ ያሉ ሰዎችን፣ ስደተኞችን፣ ጥገኝነት ጠያቂዎችን፣ በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎችን እና ዜግነት የሌላቸውን ሰዎች መብቶች በመከታተል እና ጥሰቶችን በመሰነድ ረገድ ያሏቸውን መልካም ተሞክሮዎች እና ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች አጋርተዋል። ውይይቱም ተቋማቱ በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ ሰዎች መሠረታዊ አገልግሎቶችን እና መብቶቻቸውን እንዲያገኙ በሚያደርጉት ጥረት ላይ አተኩሮ ተካሂዷል።

የብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት ዓለም አቀፍ ጥምረት ዓመታዊ ኮንፍረንስ መጋቢት 23 ቀን 2018 ዓ.ም. “በዲጂታል ምኅዳር ሰብአዊ መብቶችን በማስከበር እና በመጠበቅ ረገድ የብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት ሚና” በሚል መሪ ቃል ተካሂዷል። ኮንፍረንሱ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግ በዲጂታል ዓለም ተፈጻሚ መሆኑን በድጋሚ ያረጋገጠ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል። መግለጫው መንግሥታት የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ከግምት ውስጥ ያስገቡ አጠቃላይ የሕግ እና የፖሊሲ ማዕቀፎችን እንዲያዘጋጁም ጥሪ አቅርቧል።

ከጉባኤው ጎን ለጎን ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በጄኔቫ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት (OHCHR) የዓለም አቀፍ የሥራ ክንውን (operations) ክፍል ምክትል ዳይሬክተር አብዱል አዚዝ ቲዮዬ ጋር ተወያይተዋል። በውይይታቸውም ኢሰመኮ ሰብአዊ መብቶችን ለማስከበር እና ለማስፋፋት እያከናወናቸው ስላሉ ተግባራት እና ከከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ጋር ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል በሚችልባቸው የትብብር መስኮች ላይ ምክክር አድርገዋል።

በተጨማሪም ዋና ኮሚሽነሩ የአፍሪካ ብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት ትስስር ምክትል ሰብሳቢነትን እና የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነርነት ኃላፊነታቸውን በመጠቀም፣ አዲስ ከተቋቋመው የሶማሊያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ልዑክ ጋር ተገናኝተው እህት ተቋሙን መደገፍ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ተወያይተዋል። ውይይቱ በተለይም በተቋማዊ ዐቅም ግንባታ፣ በቴክኒክ ድጋፍ እና የልምድ ልውውጥ ጉብኝቶችን በማመቻቸት ዙሪያ ያተኮረ ነበር።