መግቢያ 

በማኅበረሰቡ ውስጥ ስለ አካል ጉዳት እና አካል ጉዳተኝነት ባለው የተሳሳተ አረዳድ ምክንያት በቅጥርና በሌሎች ከሥራ ጋር በተያያዙ ሁኔታዎች በአካል ጉዳተኞች ላይ መጠነ ሰፊ አድልዎ ይፈጸማል። ይህ ዐይነቱ አድልዎ በሁሉም የአካል ጉዳት ዐይነቶች ላይ የሚስተዋል ቢሆንም፤ በተለይም በሴት አካል ጉዳተኞች፣ ተደራራቢ አካል ጉዳት ባለባቸው እና የአእምሮ እድገት ውስንነት ባለባቸው ሰዎች ላይ ይበልጥ ተጽዕኖ ሲያሳድር ይስተዋላል።   

ይህን ታሳቢ በማድረግ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ስለ አእምሮ እድገት ውስንነት ምንነት እና በሰብአዊ መብቶች ላይ ስላለው አንድምታ ካወጣው ማብራሪያ በተጨማሪ፤ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሰዎችን ጨምሮ ስለ አካል ጉዳተኞች የሥራ መብት እንዲሁም የአእምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ሰዎች በሥራ ቦታ ሊቀርቡ ስለሚገባቸው የተመጣጣኝ ማመቻቸት (Reasonable Accommodation) እርምጃዎች ግንዛቤ ለመፍጠር ይህን ማብራሪያ አዘጋጅቷል። 

የአእምሮ እድገት ውስንነት ምንድን ነው? 

የአእምሮ እድገት ውስንነት በተባበሩት መንግሥታት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት ውስጥ ዕውቅና ከተሰጣቸው የጉዳት ዐይነቶች መካከል አንዱ ነው። ጉዳቱ በዋናነት የማሰብ/የመረዳት አቅም (cognitive functioning) እና ከሁኔታዎች ጋር የመላመድ ብቃት (adaptive functioning) ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ሲሆን፤ ይህ ዐይነቱ ጉዳት ያለባቸው ሰዎች እንደ መማር፣ ችግሮችን የመፍታት እና ውሳኔ የመስጠት ክህሎቶቻቸው እንዲሁም እንደ ተግባቦት (communication) እና ማኅበራዊ ተሳትፎ ባሉ የዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴዎቻቸው ላይ ተግዳሮት ይገጥማቸዋል።1  

የአእምሮ እድገት ውስንነት ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ነገሮችን የመረዳት፣ የመማር እና ራሳቸውን ችለው የመኖር ብቃታቸው ላይ በመመሥረት የጉዳት መጠናቸው ቀላል (mild)፣ መካከለኛ (moderate)፣ ጽኑ (severe) እና በጣም ጽኑ/ከባድ (profound) በመባል በአራት ደረጃ የሚመደብ ሲሆን2 የጉዳት መጠናቸውን ታሳቢ ያደረገ፣ ትክክለኛ ድጋፍና ስልጠና ካገኙ በሥራ ለመሰማራትና በሥራቸው ውጤታማ ለመሆን ይችላሉ።3 ምንም እንኳን ወቅታዊና የተደራጀ አኃዛዊ መረጃ ባይኖርም በኢትዮጵያ ሕፃናትን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንደሚኖሩ ይገመታል።4 

የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሰዎችን ጨምሮ ለአካል ጉዳተኞች የሥራ መብት በሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች የተሰጠው ጥበቃ ምን ይመስላል? 

የተለያዩ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ሁሉም ሰው የሚፈልገውን ሥራ በነጻነት የመምረጥ፣ ከሥራ አጥነት የመጠበቅ5፣ ፍትሐዊ እና ምቹ የሥራ እድልን በእኩልነት የማግኘት መብት እንዳለው6 እንዲሁም መንግሥት የሥራ መብት እንዲከበር እና ሁሉም ሰዎች በሥራ ራሳቸውን እንዲችሉ እና ሕይወታቸውን እንዲመሩ የማስቻል ኃላፊነት እንዳለበት ይደነግጋሉ።7 በተለይም ለአካል ጉዳተኞች መብቶች ዝርዝር እውቅና እና ጥበቃ የሚሰጠው የተባበሩት መንግሥታት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሰዎችን ጨምሮ አካል ጉዳተኞች ከጉዳት አልባ ሰዎች እኩል በነጻነት በመረጡት ወይም በሥራ ገበያ ላይ ተቀባይነት ባላቸው ሥራዎች ላይ የመሰማራት እንዲሁም አካታችና ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ በሆነ የሥራ አካባቢ ሠርቶ መተዳደሪያ የማግኘት መብት እንዳላቸው እውቅና ይሰጣል።  

በተጨማሪም ስምምነቱ መንግሥት የምልመላ መስፈርቶች፣ የቅጥር እና ሥራ፣ በሥራ ላይ የመቆየት፣ የሥራ እድገት እና ደኅንነቱ የተጠበቀና ጤናማ የሥራ ሁኔታዎችን ጨምሮ በሁሉም የቅጥር ዐይነቶች ባሉ ሁሉም ሁኔታዎች አካል ጉዳተኝነትን መሠረት ያደረገ አድሎአዊ ልዩነትን መከልከል፤ በመንግሥት የሥራ ዘርፎች አካል ጉዳተኞችን መቅጠር፤ አካል ጉዳተኞች ሥራ እንዲያገኙ፣ በሥራ ላይ እንዲቆዩና ወደ ሥራ እንዲመለሱ እገዛ ማድረግ፤ በክፍት የሥራ ገበያ ውስጥ አካል ጉዳተኞች የሥራ ልምድ እንዲያገኙ የሚያበረታቱ እርምጃዎችን መወሰድ፤ እንዲሁም አካል ጉዳተኞች እኩል የሥራ እድል እንዳያገኙ የሚያግዱ ሕጎች፣ አሠራሮች፣ ልምዶች፣ ዝንባሌዎች እንዲሁም ሌሎች ተመሳሳይ ተግባሮችን የማስወገድ ኃላፊነት እንዳለበት ያስቀምጣል።8 

ለአካል ጉዳተኞች የሥራ መብት በሀገር ውስጥ የሕግ ማዕቀፎች የተሰጠው ጥበቃ ምን ይመስላል? 

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነትን በአዋጅ ቁጥር 676/2002 ተቀብላ ያጸደቀች እንደመሆኗ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9(4) መሠረት ስምምነቱ የሀገሪቱ የሕግ አካል በመሆን የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሰዎችን ጨምሮ የአካል ጉዳተኞች የሥራ መብትን የማረጋገጥ ግዴታን በመንግሥት ላይ ይጥላል። ከዚህም በተጨማሪ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 89 (2) ሥር መንግሥት ዜጎች የኢኮኖሚ ሁኔታቸውን ለማሻሻል እኩል ዕድል እንዲኖራቸው የማድረግ ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል።   

ለአካል ጉዳተኞች የሥራ መብት ሰፊ ዕውቅና እና ጥበቃ በመስጠት ረገድ በዋናነት የሚጠቀሰው ሌላው ሀገራዊ የሕግ ማዕቀፍ የአካል ጉዳተኞች የሥራ ሥምሪት መብቶች አዋጅ ቁጥር 568/2000 ነው። አዋጁ በተለይም አካል ጉዳተኞች በተወሰኑ የሥራ መደቦች ላይ ብቻ እንዲሠማሩ ከማድረግ ይልቅ እኩል የሥራ ዕድል መርሕን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሥራው ጠባይ ወይም ባሕሪ በሚፈቅድበት እንዲሁም ተፈላጊውን የችሎታ መመዘኛ በሚያሟሉባቸው የሥራ መደቦች ሁሉ ተቀጥረው የመሥራት መብት ያላቸው መሆኑን አጽንዖት ይሰጣል። 

አዋጁ በማስታወቂያ በወጣ ክፍት የሥራ ቅጥር መደብ ላይ የተወዳደረ አካል ጉዳተኛ የወጣው የሥራ ቅጥር የሥራው ጠባይ ወይም ባሕሪ የማይፈቅድ ካልሆነ በስተቀር አስፈላጊ የችሎታ መመዘኛዎችን ካሟላ እና በውድድሩ ከፍተኛ ነጥብ ካስመዘገበ የመቀጠር መብቱ ሊጠበቅ እንደሚገባ፤ በውድድሩ ያመጣው ነጥብ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች ጋር የተቀራረበ ወይም እኩል የሆነ እንደሆነ ቅድሚያ የመቀጠር መብት ያለው መሆኑን በአንቀጽ 4 (1 እና 2) ላይ ይደነግጋል። በተጨማሪም በሥራ ዕድገት፣ በድልድል፣ በዝውውር እና በስልጠና ፕሮግራሞች ላይ አካል ጉዳተኞች ተመሳሳይ የቅድሚያ መብት እንዳላቸው ያስቀምጣል። 

የአእምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ሠራተኞች የሚወሰዱ የተመጣጣኝ ማመቻቸት እርምጃዎች ምንድን ናቸው? 

ተመጣጣኝ ማመቻቸት (reasonable accommodation) ማለት አንድ አካል ጉዳተኛ አስፈላጊ የሆኑ የሥራ ተግባራቶቹን እንዲወጣ የሚያስችሉት፣ አስፈላጊ እና ተገቢ የሆኑ የሥራ ወይም የሥራ አካባቢ ማሻሻያዎች እና ማስተካከያዎች ናቸው። የተ.መ.ድ. የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት ኮሚቴ አጠቃላይ ትንታኔ ቁጥር 2 እና 8 ላይ እንደተመለከተው የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለበትን ሰው ጨምሮ ለአካል ጉዳተኞች በሥራ ቦታ ተመጣጣኝ ማመቻቸቶች ሊቀርቡላቸው የሚገባ ሲሆን ይህ እርምጃ ለሁሉም አካል ጉዳተኞች አንድ ዐይነት ሳይሆን ከግለሰቡ ፍላጎት ጋር የተያያዘ መሆን እንዳለበት ተገልጿል። በየትኛውም ሥራ ቦታ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለበትን ሰው ጨምሮ አካል ጉዳተኞች ሥራቸውን በተሟላ መልኩ ለመሥራት የማያስችል ሁኔታ ሲገጥማቸው አሠሪው ያልተገባ ጫና የማያመጡ ተገቢ እርምጃዎችን የመውሰድ ግዴታ አለበት። ይህም ማለት አሠሪው የአእምሮ እድገት ውስንነት ካለበት ሠራተኛ ጋር በመነጋገርና ፍላጎቱን መሠረት በማድረግ ሠራተኛው ሥራውን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማከናወን የሚያስችለውን የመፍትሔ እርምጃ ዐይነት መለየትና መተግበር ነው።  

በዚህም መሠረት የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሰዎችን አስመልክቶ የግለሰቡን ፍላጎት መሠረት በማድረግ በሥራ ዐውድ ውስጥ የሚከተሉት የተመጣጣኝ ማመቻቸት እርምጃዎች9 ሊለዩና ተግባራዊ ሊደረጉ ይችላሉ። እነዚህም፦ 

  • ተግባር ተኮር ስልጠና መስጠት፦ ጉዳት ያለበትን ሰው ማዕከል ያደረገ ስልጠና መስጠት ቀዳሚው እርምጃ ነው። ይህም ሲባል የአእምሮ እድገት ውስንነት ካለበት ሰው ጋር የሥራ ግንኙነት ያላቸው የሥራ ባልደረቦች መመሪያዎችን ከአንድ ጊዜ በላይ እንዲደግሙና ጉዳቱ ያለበት ሰው ሥራውን በብቃት ማከናወን እስከሚችል ድረስ ተግባሩን በቃል ብቻ ከመግለጽ ይልቅ በተግባር እንዲያሳዩ ይጠበቃል። 
  • የቅርብ ድጋፍ የሚሰጥ አሰልጣኝ መመደብ፦ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን አዳዲስ ሠራተኞችን ለማሰልጠን ሰው መመደብ ሌላኛው የተመጣጣኝ ማመቻቸት ዐይነት ነው። ብዙ ሰዎች በአንድ ጊዜ የተወሳሰበ መመሪያ እንዲሰጧቸው ማድረግ ግራ መጋባትን ሊፈጥርባቸው ስለሚችል፤ ከአንድ ሠራተኛ ጋር በቅርበት እንዲሠሩ በማድረግ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ የሚያገኙበትን አሠራር መዘርጋት ጠቃሚ ነው። ይህም ድጋፍ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሠራተኞች በሥራ ከባቢ ውስጥ ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆንና በድንገት አደገኛ ወደሆኑ ቦታዎች እንዳይገቡ ክትትል ማድረግን ይጨምራል።  
  • ልዩ የመገናኛ ዘዴዎችን መጠቀም፦ የአእምሮ እድገት ውስንነት ካለባቸው ሠራተኞች ጋር ለመግባባት በሥራ ቦታ የተለመዱ እንደ ኢሜይል እና ደብዳቤ ያሉ መደበኛ የግንኙነት አማራጮች ይልቅ ቀለል ያሉ ቃላትን፣ አጫጭር ዓረፍተ ነገሮችን እና እንደ አስፈላጊነቱ ስዕሎችን መጠቀም ተገቢ የተመጣጣኝ ማመቻቸት ዐይነት ነው። በተለይም የአእምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ሰዎች በጽሑፍ ከሚሰጡ መመሪያዎች ይልቅ በምስል የተደገፉ ማብራሪያዎች እና ፎቶግራፎች በጣም ውጤታማ የመማሪያ መንገዶች በመሆናቸው፤ ሠራተኞች መሰል አማራጮችን እንዲተግብሩ ማበረታታት አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም፣ ጉዳቱ ያለባቸው ሰዎች የሚሠሩት ሥራ እና ቅደም ተከተሉ በየቀኑ ተመሳሳይ እንዲሆን ማድረግ የሥራ ቦታቸውን እንዲለማመዱት፣ እንግዳ ስሜት እና ድንጋጤ እንዳይሰማቸው ያግዛል።  
  • ግልጽ እና ተደጋጋሚ መመሪያ መስጠት፦ የአእምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ሰዎች የሚሰጡ የሥራ መመሪያዎች የተወሰኑ (Specific)፣ ትክክለኛ (Accurate) እና ተደጋጋሚ (Repetitive) መሆን አለባቸው። ይህም አንድን አዲስ ተግባር ለመልመድ ከተለመደው የተለየ ረጅም ጊዜ ሊወስድባቸው እንደሚችል በማሰብ በትዕግሥት ድጋፍ ማድረግን ይጠይቃል። 
  • የሠራተኞችን ግንዛቤ ማሳደግ፦ የአእምሮ እድገት ውስንነት ካለባቸው ሠራተኞች ጋር የሚሰሩ ሠራተኞች መሰል ጉዳት ካለባቸው ሰዎች ጋር የሚያደርጉትን ተግባቦት ቀላልና ተፈጥሯዊ እንዲሆን ለማስቻል ተከታታይነት ያለው ስልጠና እና ድጋፍ ማድረግ ያስፈጋል። ይህም ስለ ጉዳት ዐይነቱ ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ በማስወገድ ለሁሉም ሠራተኞች ምቹ የሥራ ከባቢን ለመፍጠር የሚያግዝ በመሆኑ ስልጠናው በተቻለ ዐቅም ለሁሉም ሠራተኞች መሰጠቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።