የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ዛሬ ግንቦት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ ቅጥር ግቢ በተካሄደ የሽልማት ሥነ ሥርዓት የአውሮፓ ኅብረት ሹማን ሽልማት (Schuman EU Awards) ስለተበረከተላቸው የተሰማውን ደስታ ይገልጻል። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ይህ ሽልማት “ዴሞክራሲን፣ የሕግ የበላይነትን፣ ሰብአዊ መብቶችን፣ መቻቻልን እና እኩልነትን በማስፋፋት ረገድ የላቀ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ሰዎች” ዕውቅና የሚሰጥ ነው።

የአውሮፓ ኅብረት ሹማን ሽልማት ለመጀመሪያ ጊዜ የተበረከተው እ.ኤ.አ. በ2017 በምያንማር የኅብረቱን 60ኛ ዓመት ምሥረታ በማስመልከት ነበር። ሽልማቱ ሰዎችን ለማበረታታት እና ተግባቦትን በማጠናከር ዲፕሎማሲን በተሻለ መንገድ ለመከወን ያለመ ነው። የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ በዝግጅቱ ላይ ባደረጉት ንግግር “የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ የአውሮፓ ኅብረትን በአንድነት ከሚያቆሙት ጉዳዮች መካከል ዋናው ነው። ሰብአዊ መብቶችን መጠበቅ እና ማስፋፋት ያለውን ጥቅም እንረዳለን። የአውሮፓ ኅብረት ፍጹም እንዳልሆኑ ቢገነዘብም የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ሂደቶቹን እና የማስፋፋት ስልቶቹን አጠናክሮ ይቀጥላል።

እንዲሁም ሰብአዊ መብቶችን በሁሉም ፕሮግራሞቻችን ውስጥ በማካተት ለተቀረው ዓለም ማስፋፋት እንፈልጋለን። የዛሬው መርኃ ግብር የዚህ ማዕቀፍ አካል ሲሆን ሕዝብን እና ግለሰቦችን ለማበረታታት ያለመ ነው” ብለዋል።

ሽልማቱ የተሰየመው እ.ኤ.አ. ከ1886 እስከ 1963 በኖረው ፈረንሳዊ ፖለቲከኛ፣ ምሁር እና አክቲቪስት ሮበርት ሹማን ስም ነው። ሮበርት ሹማን፣ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የአውሮፓውያንን እና የትራንስ አትላንቲክ ተቋማትን በመገንባት ጉልህ አስተዋጽዖ ከነበራቸው እና የአውሮፓ ኅብረትን (European Communities)፣ የአውሮፓ ምክር ቤት (Council of Europe) እና የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት (North Atlantic Treaty Organization (NATO)) መሥራቾች መካከል አንደኛው ናቸው። ስለሆነም ሽልማቱ መቻቻል እና ነጻነትን በማስፋፋት ረገድ ለተከናወኑ የላቁ ሥራዎች  ብቻ ሳይሆን፣ “እነዚህን ሁሉን አቀፍ እሴቶች በተቃውሞ እና በትችት ውስጥም ቢሆን በጽናት ለኖሩ እና ለደገፉ ከፍተኛ ስብዕና ያላቸው ሰዎች” ዕውቅና የሚሰጥ ነው።

አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ሽልማቱን ለዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ባበረከቱበት ወቅት ዶ/ር ዳንኤል የሚመሩት ኢሰመኮ ኢሰመኮ የደረጃ “A” ዕውቅና (ወይም አንደኛ ደረጃ እውቅና -“A” Status Accreditation) ያለው ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ሆኗል፤ ይህም በራሱ አስደናቂ ስኬት ነው። ኢሰመኮ አሁንም በተግዳሮቶች እና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ጭምር ድምጽ ሆኖ ቀጥሏል” ብለዋል።   

ዝግጅቱ በኢትዮጵያ የሚገኙ ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች፣ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት እንዲሁም የሀገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎች በተገኙበት ተከናውኗል።

የዘንድሮው የአውሮፓ ኅብረት የሹማን ሽልማት ከተቀበሉት መካከል:-

  • ጋሪ ኢስማኤል ዩሱፍ – የሆርሙድ የሴቶች ማኅበር መሪ፣
  • ጌቱ ሳቀታ – የአፍሪካ ቀንድ የሰብአዊ መብቶች ሊግ መሥራች፣
  • መላኩ በላይ – የፈንዲቃ የባህል ማእከል መሥራች፣
  • መልካሙ ኦጎ – የቁም ለአካባቢ ሊቀ-መንበር፣
  • የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር፣
  • ያሬድ ኃይለማርያም- የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማእከል ዋና ዳይሬክተር ይገኙበታል።

በተጨማሪም በሰብአዊ መብቶች ሥራዎቻቸው ምክንያት በእስር ቤት ውስጥ ወይም በስደት ላይ ለሚገኙ እና ይህንን ሽልማት በአካል ለመቀበል ላልቻሉ ኢትዮጵያውያን የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች በሙሉ የዕውቅና ተሰጥቷል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ለሁሉም የዘንድሮ ተሸላሚዎች የደስታ መልዕክት አስተላልፈው፣  ሽልማቱን የሚቀበሉት “ኢሰመኮ እንደ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም የተሰጠውን ኃላፊነት በተሟላ መልኩ ለመወጣት እያደረገ ላለው ጥረት ዕውቅና የሚሰጥ እና ለሕዝብ ያለብንን ኃላፊነት በትሕትና እና በቅንነት እንድንሸከም የሚያበረታታን በመሆኑ ነው” ብለዋል። አክለውም “የሰብአዊ መብቶች ሥራ መሠረት የሆኑ የሰብአዊ መብቶች መርሖች ጥያቄ ውስጥ እንዲገቡ ጫና በበዛበት እና  የሰብአዊ መብቶች ሥራን ለማከናውን የሚያስችል የሰው፣ የቴክኒክ እና የገንዘብ ሀብት ማሰባሰብ አዳጋች በሆነበት ወይም ቅድሚያ በተነፈገበት  በዚህ ወቅት ሽልማቱ መሰጠቱ ለመላው ኢትዮጵያውያንና በሀገሪቱ የሰብአዊ መብቶች እሴቶች እንዲዳብሩ በየቀኑ ለሚጥሩ ሁሉ ከፍተኛ ዕውቅና የሚሰጥ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፣ የኢሰመኮ የዘርፍ ኮሚሽነሮች ዶ/ር አብዲ ጅብሪል እና ርግብ ገብረሐዋርያን በመወከል እንዲሁም በመላው ኢሰመኮ ሠራተኞች እና በራሳቸው ስም ለዶ/ር ዳንኤል በቀለ ልባዊ የደስታ መልእክት አስተላልፈዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር እ.ኤ.አ. የ2021  “ለሰብአዊ መብቶች መከበር የሕይወት ዘመን ትግላቸው” የጀርመን አፍሪካ ሽልማትን እንዲሁም የአሊሰን ዴስ ፎርጅስ ልዩ የሰብአዊ መብቶች አክቲቪስም ሽልማትን (Alison des Forges Human Rights Award for Extra-ordinary Activism) ጨምሮ ከሌሎች ብሔራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት ዕውቅናዎችን ማግኘታቸው የሚታወስ ነው።