የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል ዓሊ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የባህል መብቶች ኮሚቴ (CESCR) አባል ሆነው በመመረጣቸው የተሰማውን ልባዊ ደስታ እየገለጸ፣ የእንኳን ደስ አለዎ መልእክቱን ያስተላልፋል። የኢትዮጵያ ይፋዊ ዕጩ የነበሩት ዶ/ር አብዲ፤ መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም. አባል ሀገራት በኮሚቴው ውስጥ ያሉትን ቀጠናዊ መቀመጫዎች ለመሙላት በኒው ዮርክ ባደረጉት ደምጽ አሰጣጥ ተመርጠዋል። ምርጫው ዶ/ር አብዲ በሰብአዊ መብቶች ዘርፍ ያላቸውን የላቀ ሙያዊ ብቃት እና ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሥርዓቶች ጋር የምታደርገውን ቀጣይነት ያለው ተሳትፎ የሚያንፀባርቅ መሆኑን ኢሰመኮ ይገነዘባል።
የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የባህል መብቶች ኮሚቴ (CESCR)፤ አባል ሀገራት ዓለም አቀፉን የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የባህል መብቶች ቃል ኪዳን (International Covenant on Economic, Social and Cultural Rights (ICESCR)) ተግባራዊ ማድረጋቸውን እንዲከታተሉ ኃላፊነት የተሰጣቸው 18 ገለልተኛ ባለሙያዎችን የያዘ አካል ነው። ቃል ኪዳኑ እንደ በቂ ምግብ፣ መጠለያ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ማኅበራዊ ዋስትና፣ ውሃና ንጽሐና እንዲሁም የሥራ መብቶችን የመሳሰሉ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የባህል መብቶች እንዲከበሩ ጥበቃ ያደርጋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ለዶ/ር አብዲ ጅብሪል ዓሊ በዚህ ስኬት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ ዶ/ር አብዲ ያላቸው የላቀ ሙያዊ ብቃት፣ ገለልተኝነት እና የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የባህል መብቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስከበር ባላቸው ቁርጠኝነት ላይ ሙሉ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም ይህ ስኬት ኢትዮጵያ እና ኢሰመኮ ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሥርዓቶች፣ በተለይም ከተባበሩት መንግሥታት የስምምነት አስፈጻሚ አካላት (Treaty Bodies) ጋር ያላቸውን የሥራ ግንኙነት እንደሚያጠናክር አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል። ኢሰመኮ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያለውን ትብብር በማጠናከር፣ ሪፖርቶችን በማቅረብ እና የምክረ ሐሳቦችን አፈጻጸም በመከታተል በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች እንዲስፋፉ፣ እንዲጠበቁ እና ደረጃዎች እንዲተገበሩ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። በመጨረሻም ዋና ኮሚሽነሩ ለዶ/ር አብዲ በአዲሱ ዓለም አቀፍ ኃላፊነታቸው ስኬታማ የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።