የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በዳኝነት ነጻነት እና ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እንዲሁም በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ እና የፍትሕ ዘርፍ ሪፎርም ዙሪያ ከማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፍትሕ አካላት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ዳኞች ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ሰኔ 20 ቀን 2018 ዓ.ም. በሆሳዕና ከተማ አካሂዷል። በመድረኩ የክልሉ ዋና አፈ ጉባኤ ክብርት ፋጤ ስርሞሎ እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት እርሴኖ አቡሬን ጨምሮ የተለያዩ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች አስተዳዳሪዎች፣ የክልሉ የፍትሕ ዘርፍ ተቋማት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።





በመድረኩ በዳኝነት ነጻነት እና ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ፣ የዳኝነት ተቋማት ሰብአዊ መብቶችን ከማስከበር አንጻር ያላቸው ሚና እንዲሁም በሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ዙሪያ የተዘጋጁ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተድርጎባቸዋል። የሕግ የበላይነትን ለማስከበር፣ ሰብአዊ መብቶችን ለማስጠበቅ እና የፍትሕ ተቋማት በሕዝብ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት እና አመኔታ ለማሳደግ ነጻ የዳኝነት ሥርዓት አስፈላጊ መሆኑ ተነስቷል። በተጨማሪም ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ፣ ተጎጂዎችን ለመካስ እንዲሁም ዘላቂ ሰላም እና እርቅን ለማስፈን ተአማኒ፣ አካታች እና ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ የሽግግር ፍትሕ ትግበራ ወሳኝ መሆኑ ተብራርቷል።

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ክብርት ፋጤ ስርሞሎ ኢሰመኮ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩን ማዘጋጀቱ በክልሉ ያለውን የፍትሕ አካላት ዐቅም ለማጠናከር እንደሚረዳ ገልጸዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ጠንካራ ተቋማዊ አጋርነትን በመመሥረት እና ቀጣይነት ያለው የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራዎችን በመሥራት፣ ነጻ እና ተጠያቂነት የሰፈነበት የፍትሕ ሥርዓት መገንባት እንደሚቻል አንስተው በክልሉ ያሉ የፍትሕ ተቋማትን ለማጠናከር እና የሰብአዊ መብቶች ጥበቃን ለማሻሻል የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።