የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በታኅሣሥ እና በጥር ወራት 2013ዓ.ም. በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ ይፋ ባደረጋቸው ሪፖርቶች፣ ኮሚሽኑ ገና በአካል ተገኝቶ ምርመራ ለማድረግ ባልቻለባቸው የትግራይ ክልል አካባቢዎች በጦርነቱ ሂደት የሲቪል ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ የአካላዊ እና ሥነልቦናዊ ጉዳት መድረሱን፣ ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት፣ ዘረፋ እና ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ስለመፈጸማቸው መረጃዎች እንደደረሱት ጠቅሶ፣ በእነዚህ አካባቢዎች ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ሰብአዊ ቀውስ እና የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ በመመርመር ላይ የሚገኝ መሆኑን ማሳወቁ ይታወሳል። እንዲሁም ኢሰመኮ በየካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጠው ምላሽ በአክሱም ስለተፈጸመው ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጾ፣ በከተማዋ ላይ ተካሂዶ የነበረው ውጊያና ወታደራዊ ጥቃት ስላደረሰው ጉዳትና ኤርትራውያን ወታደሮች በሲቪል ሰዎች ላይ ጥቃት እንዳደረሱ መረጃዎች እንደደረሱትም አሳውቆ ነበር።
በዚህም መሰረት፣ ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ወደ አክሱም ለመጓዝ ያደረገው ጥረት በፀጥታ ሁኔታውና በተያያዥ ምክንያቶች ሳይሳካ ቢቆይም፣ ከየካቲት 20 እስከ የካቲት 26 ቀን 2013ዓ.ም. ድረስ በአክሱም ከተማ በመገኘት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን፣ 45 የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ የዓይን እማኞችን እና የሃይማኖት መሪዎችን አነጋግሯል። እንዲሁም 20 ሰዎች የተሳተፉበት የቡድን ውይይት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር አድርጓል። በተጨማሪም ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ ከአክሱም ቅድስት ማርያም ሆስፒታል፣ ከአክሱም ሪፈራል ሆስፒታል፣ ከሚመለከታቸው የቀበሌ መስተዳደር አካላት እንዲሁም ከሃይማኖት ተቋማት አገልጋዮች የተለያዩ የምስል፣ የድምጽ እና ሌሎች ሰነዶችን አሰባስቧል ። ኮሚሽኑ የአክሱም ከተማ ከንቲባን እና ምክትል ከንቲባን በዚህ የምርመራ ጉቡኝት ወቅት ለማግኘት ያደረገው ጥረት ባይሳካም፤ ወደፊት በሚደረጉ የምርመራ ጉብኝቶች የሚመለከታቸውን ወታደራዊና ሲቪል ኃላፊዎች በሙሉ እንደሚያገኝ እምነት አለው።
የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱን ከዚህ በታች ይመልከቱ፡ https://ehrc.org/wp-content/uploads/2021/05/በትግራይ-ክልል፣-አክሱም-ከተማ-የተፈጸመው-ከፍተኛ-የሰብአዊ-መብቶች-ጥሰት-ምርመራ-ሪፖርት-3.pdf