የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ባከናወናቸው የሰብአዊ መብቶች ክትትሎች የተለዩ ግኝቶች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ላይ ሚያዚያ 29 ቀን 2018 ዓ.ም. በባምባሲ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የሕግ እና ፍትሕ አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ፣ ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እና ከተለያዩ ዞኖች፣ ወረዳዎች፣ ልዩ ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያዎች የተወጣጡ ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በውይይቱ ኢሰመኮ በፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ባከናወናቸው ክትትሎች የተለዩ አዎንታዊ እና አሳሳቢ ጉዳዮች እንዲሁም የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ከሕግ አግባብ ውጪ የሚደረጉ እስሮች እና የቤተሰብ ጉብኝት ክልከላዎች ላይ መሻሻሎች መኖራቸው፤ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የማቆያ ስፍራዎች እደሳት እና አዲስ የማስፋፊያ ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆኑ እንዲሁም የተወሰኑ ፖሊስ ጣቢያዎች በእስር ላይ ለሚገኙ ተጠርጣሪዎች ምግባ የሚውል በጀት መያዝ መጀመራቸው በውይይቱ በአዎንታዊነት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል፡፡

በሌላ በኩል የተጠርጣሪዎችን መብቶች በማያከብሩና የመብት ጥሰት በሚያደርሱ የፖሊስ አባላት ላይ አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃዎችን አለመወሰድ፤ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰዎችን ማሰር፤ በሕግ በተቀመጠው ቀነ ገደብ ፍርድ ቤት አለማቅረብ፤ ከሕግ አግባብ ውጪ የሚደረጉ አፈሳ/ የጅምላ እስሮች መኖር፤ የማቆያ ክፍሎች ጥበትና የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር በክልሉ አንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች በአሳሳቢነት የቀጠሉ እና ሊሻሻሉ የሚገባቸው ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በአሳሳቢነት የቀጠሉ ችግሮችን ለማሻሻል እና በክልሉ ያለው አጠቃላይ የተጠርጣሪዎች አያያዝ ሁኔታ ሰብአዊ መብቶችን ያከበረ እንዲሆን አበክሮ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የኢሰመኮ የክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል ሪጅናል ዳይሬክተር በጋሻው እሸቱ በጥበቃ ስር ያሉ ሰዎችን ሰብአዊ መብቶች በማክበር፤ በማስከበር እና በማሟላት ረገድ የፖሊስ ተቋማት ትልቅ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን አንስተው የኢሰመኮ ምክረ ሐሳቦችን ተግባራዊ ማድረግን ጨምሮ በክልሉ ያለው የተጠርጣሪዎች አያያዝ ሁኔታ ሰብአዊ መብቶችን ያከበረ መሆኑን ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡