የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ አድሎአዊ የዘር ልዩነቶችን ለማስወገድ የተደረገ ዓለም አቀፍ ስምምነት (International Convention on the Elimination of All Forms of Racial Discrimination (ICERD)) አፈጻጸም ዙሪያ በተዘጋጀው የተጠቃለለ (ከ 17ኛ እስከ 25ኛ) ወቅታዊ ሪፖርት ረቂቅ ላይ ሰኔ 5 ቀን 2018 ዓ.ም. የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ አካሂዷል። የምክክር መድረኩ ዐላማ ባለድርሻ አካላት ሀገሪቱ ስምምነቱን (ICERD) በመተግበር ረገድ ያስመዘገበቻቸውን አዎንታዊ ውጤቶች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንዲሁም የተስተዋሉ ክፍተቶችን በመገምገም ገንቢ አስተያየቶችን እና ግብዓቶችን እንዲሰጡና በሪፖርት ዝግጅት ሂደቱ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማስቻል ነው።

የሪፖርት ዝግጀት ሂደቱ አካታች እና አሳታፊ መሆኑን ለማረጋገጥ በመድረኩ ከሪፖርት ዝግጅት ቡድኑ (ከተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተወጣጣ ቡድን)፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ከተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ ከመንግሥት ኤጀንሲዎች እና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተወጣጡ ተወካዮች ተሳተፈዋል። በተጨማሪም ተሳታፊዎች ስለ ስምምነቱ ዋና ዋና ይዘቶች እና አድሎአዊ የዘር ልዩነቶችን የማስወገድ ኮሚቴ (Committee on the Elimination of Racial Discrimination (CERD)) ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2008 ያቀረበችውን የቀድሞ ሪፖርት በመገምገም እ.ኤ.አ. በ2009 በሰጠው የማጠቃለያ አስተያየቶች ላይ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተደርጓል።

በምክክር መድረኩ በነበሩ የቡድን ውይይቶች ተሳታፊዎች በረቂቅ ሪፖርቱ ላይ ያላቸውን አስተያየት እና ስጋት ያካፈሉ ሲሆን ረቂቅ ሪፖርቱን ለማጠናከር እና በመጨረሻ የሚቀርበው ሪፖርት ይዘትን ለማጎልበት የተሰጡ ሁሉም ግብዓቶች በረቂቅ ሪፖርቱ አዘጋጅ ቡድን እና በፍትሕ ሚኒስቴር በጥንቃቄ ተመዝግበዋል።

በፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የዓለም አቀፍ ትብብር ዳይሬክተር ዩሱፍ ጀማው፣ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሪፖርቶችን ጊዜውን ጠብቃ የማቅረብ ግዴታ እንዳለባት አጽንዖት ሰጥተው፤ ሪፖርት የማቅረብ ሂደት የሀገሪቱን የሰብአዊ መብቶች ግዴታዎች አፈጻጸምን ለመገምገም አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል። በተጨማሪም፣ ዘግይቶ የነበረውን የተጠቃለሉ (ከ17ኛ እስከ 25ኛ) ሪፖርቶች ረቂቅ የዝግጅት ሂደት እና በሂደቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን አስመልክቶ ገለጻ ሰጥተዋል።

የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶክተር አብዲ ጅብሪል፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች አፈጻጸምን ለመገምገም ሪፖርት የማቅረብ ግዴታዎችን በየጊዜው መወጣት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፣ ለአድሎአዊ የዘር ልዩነቶችን የማስወገድ ኮሚቴ (CERD) የሚቀርበው የኢትዮጵያ ሪፖርት ለረጅም ጊዜ መዘግየቱን አስታውሰዋል። አክለውም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና የመንግሥት ተቋማት በብሔራዊ ሪፖርት ዝግጅቱ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በስምምነቱ አፈጻጸም ላይ የራሳቸውን ገለልተኛ ወይም ተጨማሪ ሪፖርት ማቅረብ መብት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።