የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ለመግለጽ ይወዳል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም በኢትዮጵያ ካሉት ታላላቅ የሰብአዊ መብቶች ተሟጓቾች አንዱ ሆነው በታሪክ ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡

ፈር ቀዳጅ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች የነበሩት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ለበርካታ አስርት ዓመታት የማይናወጥ ቁርጠኝነት የተሞላበት ሕይወት ከመኖራቸው ባሻገር ብዙውን ጊዜ እስራትን የሚጨምር ከባድ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም የአገሪቱ አንጋፋው የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ መስራች አባልም ነበሩ፡፡


የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ(ዶ/ር) “ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም አንጋፋ ምሁር ፣ መምህር ፣ የታሪክ አዋቂ እና ፖለቲከኛ ከመሆናቸውም በላይ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ጀግና ተብለው ለዘላለም የሚታወሱ ፣ የማይፈሩ እና ቁርጠኛ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ነበሩ” ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ ለፕሮፌሰር መስፍን ቤተሰቦች እና ለወዳጆች በሙሉ ከልብ የመነጨ መጽናናትን ይመኛል፡፡