የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከኢሰመኮ-ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የትብብር መድረክ የሽግግር ፍትሕ ንዑስ ቡድን አባላት ጋር በመተባበር፤ ከባድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተጎጂዎች እውነትን የማወቅ መብት እና ክብር ዓለም አቀፍ ቀንን አስመልክቶ መጋቢት 15 ቀን 2018 ዓ.ም የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ አዘጋጅቷል። ውይይቱ ባለድርሻ አካላት እውነትን የማወቅ መብት በሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ ያለውን ወሳኝ ሚና እንዲገነዘቡ ለማድረግ ያለመ ሲሆን፣ ተጎጂዎች፣ የሽግግር ፍትሕ ባለሙያዎች እንዲሁም ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ከተጎጂዎች ማኅበራት እና ከልማት አጋሮች የተወጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።





በመድረኩ እውነትን የማወቅ መብት ተጠያቂነት ለማረጋገጥ፣ እርቅን ለማውረድ እና ወደፊት ተመሳሳይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ዳግም እንዳይከሰቱ ለመከላከል ያለውን ፋይዳ በተመለከተ ዝርዝር ገለጻ ቀርቧል። በተለይም ተጎጂዎች እና ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች በሽግግር ፍትሕ ሂደት ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
በተጨማሪም በስቲቭ ዮርክ የተዘጋጀ እና በጆሴፍ ዊድንማየር የተቀናበረ “Confronting the Truth” (እውነትን መጋፈጥ) የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ለእይታ የቀረበ ሲሆን፣ ይህም ተሳታፊዎች ስለ እውነት አፈላላጊ ኮሚሽኖች ሚና፣ በእውነት፣ በፍትሕና በተጠያቂነት መካከል ስላለው ግንኙነት፣ እንዲሁም እውነትን በመፈለግ ጥረቶች ውስጥ የተጎጂዎችና ከጉዳት ያገገሙ ሰዎች ተሳትፎ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው አድርጓል።






የውይይቱ ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ማዕቀፍ እውነትን የማፈላለግ ኃላፊነት ያለባቸው አካላት ሂደቱ ግልጽነት ያለው፣ ምላሽ ሰጪ እና በሰብአዊ መብቶች መርሖች ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ የተጎጂዎችን እና የተጎጂ ማኅበረሰቦችን የሕይወት ተሞክሮና ፍላጎት የሚያንጸባርቅ፣ አካታችና አሳታፊ በሆነ መልኩ ሊቀረጽ እንደሚገባም አሳስበዋል። አክለውም ተጎጂዎች ለደረሰባቸው ጉዳት እውቅና ከመስጠት ባለፈ፣ የፍትሕ ሂደቶችን በመቅረጽ ረገድ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድርግ ለሂደቱ ውጤታማነት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢሰመኮ የዋና ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ቃልኪዳን ደረጄ እውነትን ማውጣትና እውቅና መስጠት ለማኅበረሰባዊ እርቅ የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ የሽግግር ፍትሕ ላለፉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የሕግ ምላሽ ከመስጠት ባለፈ ክብርን የመመለስና በማኅበረሰቦች መካከል እምነትን የመገንባት ሥራ መሆኑን አስገንዝበዋል። አክለውም ኢሰመኮ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ለተጎጂዎች የሚደረጉ ድጋፎች እንዲቀጥሉና መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶች በስፋት እንዲከናወኑ አበክሮ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።