በዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አደሎ የተመራው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፤ ከጥር 27 እስከ 29 ቀን 2018 ዓ.ም. በያውንዴ፣ ካሜሩን በተካሄደው የአፍሪካ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ትስስር (NANHRI) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እና ጠቅላላ ጉባኤ እንዲሁም ትስስሩ በየሁለት ዓመቱ በሚያዘጋጀው 15ኛው ጉባኤ ላይ ተሳትፏል።



በአፍሪካ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ትስስር (NANHRI) የሕግ ማዕቀፍ አንቀጽ 56 መሠረት በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደውዊ ጉባኤ በተለያዩ የአፍሪካ ቀጠናዎች መካከል በፈረቃ የሚስተናገድ ሲሆን፤ በ2019/20 ዓ.ም. (እ.አ.አ በ2027) የሚካሄደውን የትስስሩን ጉባኤ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና እንደሚያስተናግድ ይጠበቅ ነበር። በዚህም በጠቅላላ ጉባኤው ስብሰባ ወቅት ኢሰመኮ የትስስሩን 16ኛ ዓመታዊ ጉባኤ እና የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ እንዲያስተናግድ በሙሉ ድምፅ ተመርጧል። ይህ ውሳኔ ኢሰመኮ የጥምረቱ ምክትል ሰብሳቢ እንዲሆንም አድርጎታል። ኢሰመኮ የፓሪስ መርሖችን ሙሉ በሙሉ አክብሮ የሚሠራ “ደረጃ-ሀ” (A-status) ያለው የምሥራቅ አፍሪካ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም በመሆኑ እና የትስስሩን አባልነት ግዴታዎች በአግባቡ በመወጣቱ ጉባኤውን ለማስተናገድ የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን ሙሉ በሙሉ እንዲያሟላ አስችሎታል።
ኢሰመኮ በሙሉ ድምፅ መመረጡ የትስስሩ አባል ተቋማት በኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ቁርጠኝነት ላይ ያላቸውን ጠንካራ እምነት እና የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል በሆነችው አዲስ አበባ በርካታ የሰብአዊ መብቶች ባለሙያዎችን የሚያሳትፍ ታላቅ ጉባኤ የማደራጀት ዐቅም እንዳለው አሳይቷል።


ይህ ጉባኤ አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማትን፣ የአፍሪካ ሕብረት የሰብአዊ መብቶች አካላትን፣ የሲቪል ማኅበራትን፣ የሰብአዊ መብቶች ባለሙያዎችን፣ ተመራማሪዎችን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማገናኘት በአህጉሪቱ አንገብጋቢ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ እንዲመክሩና የጋራ የትብብር አቅጣጫዎችን እንዲቀይሱ ዕድል ፈጥሯል።
በተጨማሪም ኢሰመኮ በንግድ እና ሰብአዊ መብቶች (Business and Human Rights) ዘርፍ እያደረገ ያለውን ንቁ ተሳትፎ እና የኢትዮጵያን ብሔራዊ የድርጊት መርሃ ግብር ረቂቅ በማዘጋጀት ረገድ እያበረከተ ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት አዲስ በተቋቋመው የትስስሩ “የንግድ እና ሰብአዊ መብቶች የሥራ ቡድን” ውስጥ በአባልነት ተመርጧል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አደሎ ጉባኤውን የአፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ዋና ቢሮዎች መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ ማካሄዱ ትስስሩ ቁልፍ መልእክቶቹን ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቀጥታ ለማድረስ እና የላቀ ተጽዕኖ ለመፍጠር እንደሚያስችለው ገልጸው ኢሰመኮ ከትስስሩ እና ከአባል ተቋማቱ ጋር በመተባበር 16ኛውን ዓመታዊ እና ጠቅላላ ጉባኤ በስኬት ለማስተናገድ ዝግጁ እና ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።