የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት (United Nations Office of the High Commissioner for Human Rights (OHCHR)) እና ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከየካቲት 9 እስከ 12 ቀን 2018 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ዐውደ ጥናት አካሂዷል። የዐውደ ጥናቱ ዓላማ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና የብሔራዊ ተቋማት (National Mechanisms) አድሎአዊ የዘር ልዩነቶችን ለማስወገድ የተደረገ ዓለም አቀፍ ስምምነት (International Convention on the Elimination of All Forms of Racial Discrimination (ICERD) አፈጻጸም የመከታተል እና ሪፖርት የማቅረብ ዐቅማቸውን ማጠናከር ነው፡፡

የዐውደ ጥናቱ አጠቃላይ ግብ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በንቃት በማሳተፍ ለኢትዮጵያ የተሰጡ የዓለም አቀፍ ስምምነት አስፈጻሚ አካል ምክረ ሐሳቦች (treaty body recommendations) አፈጻጸም ላይ የሚደረገውን ክትትል ማሻሻል እና የዘገዩ ሪፖርቶች የሚቀርቡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። በዐውደ ጥናቱ የተለያዩ የሲቪል ማኅብረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች እና የብሔራዊ የሪፖርት አቀራረብ እና ክትትል ሥርዓት (National Mechanism for Reporting and Follow-up (NMRF) የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ፣ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት እና ከፍትሕ፣ ከውጭ ጉዳይ፣ ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ፣ ከትምህርት እንዲሁም ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በተካሄዱት የውይይት ክፍለ ጊዜዎች፣ የሀገራት ሪፖርት የማቅረብ ግዴታዎች እና የኢትዮጵያ አሁናዊ የሪፖርት አቀራረብ ሁኔታ እንዲሁም ኢትዮጵያ በ2001 ዓ.ም. ያቀረበችውን ሪፖርት ተከትሎ አድሎአዊ የዘር ልዩነቶችን የማስወገድ ኮሚቴ (Committee on the Elimination of Racial Discrimination (CERD)) በ2001 ዓ.ም. የሰጣቸው የመደምደሚያ ምልከታዎች (concluding observations) ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። ተሳታፊዎችም በሪፖርት አቀራረብና በክትትል ሂደት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚናን ያነሱ ሲሆን፣ አድሎአዊ የዘር ልዩነቶችን ለማስወገድ የተደረገውን ዓለም አቀፍ ስምምነት አፈጻጸም በተመለከተ በፍትሕ ሚኒስቴር እየተዘጋጀ ስላለው ረቂቅ ሪፖርት መረጃ ተሰጥቷቸዋል። በዐውደ ጥናቱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሪፖርት አቀራረብ ሂደት ውስጥ ያላቸው ወሳኝ ሚናን ጨምሮ አማራጭ ሪፖርቶችን ማቅረብ፣ በመንግሥት በሚመሩ የምክክር መድረኮች ላይ መሳተፍ እንዲሁም ለኮሚቴው መደበኛ ያልሆኑ መግለጫዎችን እና ወቅታዊ መረጃዎችን መስጠት ጨምሮ ትኩረት ተሰጥቶታል።

የሲቪል ማኅበራቱ የአድሎአዊ የዘር ልዩነቶችን ለማስወገድ በተደረገው ዓለም አቀፍ ስምምነት ውስጥ በተካተቱ የተወሰኑ ድንጋጌዎች እና ኮሚቴው በ2001 ዓ.ም. በሰጣቸው የመደምደሚያ ምልከታዎች (concluding observations) ላይ የቡደን ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የስምምነቱን አፈጻጸም በሚመለከት የተስተዋሉ አዎንታዊ ለውጦችን እና ትኩረት የሚሹ አሳሳቢ ጉዳዮችን ለይተዋል።

ዐውደ ጥናቱ በሪፖርት አዘገጃጀት እና አቀራረብ ሂደቶች ውስጥ ያሉ የተለያዩ የተሳትፎ ደረጃዎችን በሚመለከት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ግንዛቤ ያሳደገ ሲሆን፤ ይህም መንግሥት ሪፖርቱን ከማቅረቡ በፊት፣ ኮሚቴው ግምገማ በሚያደርግበት ጊዜ፣ የመደምደሚያ ምልከታዎች ከጸደቁ በኋላ እንዲሁም በራሳቸው አማራጭ ሪፖርቶች በማቅረብ፣ ትግበራን በመከታተል፣ ለውጦች እንዲደረጉ በመወትወት እና ግንዛቤን በማሳደግ ረገድ ያሏቸውን ሚናዎች ያካትታል።

በዐውደ ጥናቱ የብሔራዊ የሪፖርት አቀራረብ እና የክትትል ሥርዓት የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚቴ ኢትዮጵያ በ2001 ዓ.ም. አድሎአዊ የዘር ልዩነቶችን ለማስወገድ የተደረገውን ዓለም አቀፍ ስምምነት አፈጻጸም በተመለከተ ሪፖርት ካቀረበች በኋላ የነበረውን የ17 ዓመታት ጉዞ በተመለከተ በኅዳር ወር 2018 ዓ.ም. በተካሄደ ዐውደ ጥናት በመረጃ አሰባሰብ ሂደት ላይ ያጋጠሙ ችግሮች እና የታዩ መሻሻሎች ላይ ውይይት አድርጓል፡፡ ኮሚቴው የተሟላ ረቂቅ ሪፖርት ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉ ቅደም ተከተሎችን እና የጊዜ ሰሌዳን በያዘው ፍኖተ ካርታ መሠረት፣ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተሰበሰቡ መረጃዎችን በማጠናቀር ከባለድርሻ አካላት ጋር ለሚካሄድ ተጨማሪ ውይይት እና ምክክሮች የመጀመሪያ ረቂቅ ሪፖርት አዘጋጅቷል።