የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ጥቅምት 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ያደረገውን ሁለተኛውን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች ሁኔታ ሪፖርት በሚመለከት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የኮሚሽኑ ሪፖርት በጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው የነበሩ የትግራይ ክልል ተፈናቃዮች በብዛት ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው እንደተመለሱ እና ሰብአዊ ድጋፍ እየቀረበላቸው እንደሆነ ተደርጎ የተገለጸው ስሕተት ስለሆነ ሊስተካከል ይገባል በሚል መግለጹን ተከትሎ፣ ኢሰመኮ ወዲያውኑ በሰጠው አጭር ማብራሪያ ሪፖርቱ ይህንን መሰል መረጃ እንደማያካትት፣ የሪፖርቱ አካባቢያዊ ወሰን የትግራይ ክልልን እንደማይጨምር በሪፖርቱ የተገለጸ መሆኑንና በተሳሳተ አረዳድ ስለተሰራጨው የተሳሳተ መረጃና ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ ኮሚሽኑ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር እንደሚነጋገር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በዚህም መሠረት ኮሚሽኑ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ጋር የተነጋገረ ሲሆን፣ ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች ሁኔታ ሪፖርቱ ከሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. እስከ ሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ እና በአፋር፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማእከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ሶማሊ ክልሎች የሚሸፍን መሆኑን አስረድቷል (ገጽ 8)። ስለሆነም የትግራይ ክልል በሪፖርቱ የተሸፈነ አለመሆኑን በድጋሚ ለማስረዳትና ለማሳወቅ ተችሏል። ስለሆነም የትግራይ ክልል በሪፖርቱ የተሸፈነ አለመሆኑን በድጋሚ ማሳወቅ ተችሏል።
የትግራይ ክልል በዚህ የጊዜ ወሰን ሊካተትበት ያልቻለበት ምክንያት ሪፖርቱ በተጠናቀረበት ወቅት ክልሉ በጦርነት ሳቢያ ተደራሽ ስላልነበር፣ እንዲሁም የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ የሚሸፍን ሌላ የክትትል ሥራ እየተካሄደ በመሆኑ እና ከዚህ ጋር ተያያዥ በሆኑ ምክንያቶች ነው። በተጨማሪም ሪፖርቱ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ተፈናቅለው የነበሩ በርካታ ሰዎች ወደቀያቸው የተመለሱ መሆኑን የተገለጸው ምንም እንኳን አተገባበሩ ላይ ክፍተት ቢኖርበትም በጦርነቱ ምክንያት ከአፋር እና አማራ ክልሎች ተፈናቅለው የነበሩትን ሰዎች የሚመለከት ነው።
ሪፖርቱ በግጭት እና በሌሎች ሰው ሠራሽ መንሥዔዎች የተፈናቀሉ ከ369 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን፣ ተመላሾችን እና ወደ ሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ የተደረጉ ተፈናቃዮችን የሚያስጠልሉ 62 መጠለያዎችን፣ ጣቢያዎችን እና ተቀባይ ማኅበረሰቦችን በመድረስ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ አያያዝ ላይ ክትትሎች እና ምርመራዎችን በማካሄድ የተጠናከረ ነው። ኢሰመኮ በትግራይ እና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን እና ስደተኞችን በተመለከተ በተደጋጋሚ የሰብአዊ ድጋፍ ጥሪ እና ተያያዥ ጉዳዮች በአፋጣኝ ትኩረት እንዲሰጣቸው የመንግሥት እና የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብን ሲወተውት መቆየቱ ይታወሳል።
ኮሚሽኑ ይህንኑ የሚያደርገውን ክትትል እና ጥረት እንደሚቀጥል አስታውሰው፣ የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ “በሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራ፣ በተለይም በወቅታዊው አስቸጋሪማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ዐውድ እንዲሁም የማኅበራዊ ሚዲያ ነባራዊ ሁኔታ ይህን መሰል የተሳሳቱ አረዳዶች፣ እንዲሁም ሆን ተብለው የሚሰራጩም የተሳሳተ መረጃዎች ሊያጋጥሙ የሚችሉ ናቸው። ሆኖም ኮሚሽኑ በተቻለ ዐቅም እና የጸጥታ ሁኔታው በፈቀደ ጊዜ ሁሉ ተደራሽ በሆነ መልኩ የሚያደርገውን የምርመራ እና ክትትል ሥራ የሚቀጥል ነው” ብለዋል።
በተጨማሪም ኮሚሽኑ ከጦርነቱ ወቅት ጀምሮ በትግራይ ክልል ሲያከናውን የነበረው መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ሥራዎች በኮሚሽኑ ድረገጽ ላይ የሚገኙ መሆኑን አስታውሰው ከዚህ ውጭ የሚሰጡ የተሳሳቱ መረጃዎች ተገቢ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በትግራይ ክልል ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በተመለከተም ኢሰመኮ ሲያከናውን የቆየው ክትትል ሪፖርት ላይ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተለያዩ ዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ምላሽ የተገኘ መሆኑን ገልጸው፣ ተገቢው ሂደት እንደተጠናቀቀ ሪፖርቱ የሚቀርብ መሆኑን አስታውቀዋል።