የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ዐይነ ሥውራን ማኅበር እና ከተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ አህጉራዊውን በአፍሪካ የሰዎች እና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር የአካል ጉዳተኞች መብቶች ፕሮቶኮል (የአፍሪካ የአካል ጉዳተኞች ፕሮቶኮል) የምታጸድቅበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ያለመ ውይይት ሰኔ 15 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አካሂዷል። በመድረኩ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ሕግና ፍትሕ ኢኒስቲትዩት፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአካል ጉዳተኞች ማኅበራት እና ከሌሎች ባለድርሻዎች የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

በውይይቱ የአፍሪካ የአካል ጉዳተኞች ፕሮቶኮል ይዘት፣ ዓላማዎች እና ፕሮቶኮሉ ለአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ያለው አስተዋጽዖ በስፋት ቀርቧል። ፕሮቶኮሉ ከተባበሩት መንግሥታት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት ጋር ያለው ተዛማጅነትና ልዩነት እንዲሁም በኢትዮጵያ ዐውድ በአካል ጉዳተኞች የሚሰጣቸው ጥበቃዎች በዝርዝር ቀርቧል። ከፕሮቶኮሉ ልዩና አዳዲስ ይዘቶች መካከል አካል ጉዳት ያለባቸው ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ሕፃናት እና አረጋውያን ለመብቶች ጥሰት በሚያጋልጥ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን እውቅና የሰጠ መሆኑ፤ በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚፈጸሙ አድልዎና ጥቃቶችን እንዲሁም ከማኅበረሰብ ማግለልን የመሳሰሉ ኋላ ቀር ድርጊቶችን ለማስወገድ የሚያግዝ ሰፊ የጥበቃ ማዕቀፍ የዘረጋ መሆኑ፤ የባሕል ፍርድ ቤቶች ፍትሕ ከማግኘት መብት አኳያ ያላቸውን ሚና እንዲሁም መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ቁልፍ የግንኙነት አማራጭ ለሆነው የምልክት ቋንቋና ተያያዥ የጋራ እምነቶች እና እሴቶች (deaf culture) እውቅና የሚሰጥ መሆኑ ተጠቃሽ ናቸው። በተጨማሪም፣ አካል ጉዳተኞች ለድኅነት እና ተያያዥ ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች ያላቸውን ተጋላጭነት፣ የማኅበረሰብ አቀፍ እንክብካቤ እና ድጋፍ አገልግሎት አስፈላጊነትን ዕውቅና የሰጠ መሆኑ ተብራርቷል።

ፕሮቶኮሉ አህጉራዊና ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ያገናዘበ የሕግ ማእቀፍ የሚዘረጋ ከመሆኑም ባሻገር የአካል ጉዳተኞች መብቶችን በኢትዮጵያ ለማሟላት የሚደረጉትን እንቅስቃሴዎች ለማጠናከር፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል እና አድሏዊ አመለካከቶችና አሠራሮችን ለማሻሻል የሚያግዙ ግብዓቶችን መያዙ ጠቀሜታው ከፍ ያለ መሆኑ በመድረኩ ተነስቷል። በተጨማሪም በፕሮቶኮሉ የተቀመጡ ግዴታዎችን ለማሟላትና አተገባበራቸውን ለመከታተል ካሉት ነባር ተቋማት ውጪ ሌላ አዲስ አስፈጻሚ አካል ማቋቋም የማይጠይቅ መሆኑ ተመላክቷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ኢትዮጵያ ፕሮቶኮሉን በማጽደቅ ልታገኘው የምትችለው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ጠቀሰው፣ የአካል ጉዳተኞችን ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ለማጠናከር፣ የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፎችን ለማሻሻል፣ እንዲሁም የአካታች ልማት እና ተሳትፎን ለማበረታታት ፕሮቶኮሉ በፍጥነት ሊጸድቅ እንደሚገባ አመላክተዋል።

የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር መሐመድ አሕመድ በተግባር ላይ ያሉ የሕግ ማዕቀፎች እንዳሉ ሆነው፣ የአፍሪካ የአካል ጉዳተኞች ፕሮቶኮልን ማጽደቅ ለአካል ጉዳተኞች መብቶች መከበር ተጨማሪ ዐቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል። አክለውም አህጉራዊ ስምምነቱን የማጽደቅና ወደ ተግባር እንዲገባ የማድረግ ሥራ የሁሉንም ባለድርሻዎች ተሳትፎና ቁርጠኛ አቋም የሚጠይቅ በመሆኑ ጅምር ሂደቶችን በማጠናቀቅ ፕሮቶኩልን በፍጥነት ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ ተግባራዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አሳስበዋል።

የአፍሪካ የአካል ጉዳተኞች ፕሮቶኮል እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 28፣ 2018 (ጥር 20 ቀን 2010 ዓ.ም.) የጸደቀ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ. ከጁላይ 5፣ 2024 (ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም.) አንስቶ ስምምነቱ በሁሉም ፈራሚ ሀገራት ውስጥ አስገዳጅ እንዲሆን እና ወደ ተግባር እንዲገባ የሚያስችለውን የፈራሚ ሀገራት ቁጥር በማግኘቱ ወደ ሥራ ገብቷል። አህጉራዊው ስምምነት ባለፉት 8 ዓመታት ውስጥ በ17 ሀገራት የጸደቀ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ስምምነቱን እስካሁን አላጸደቀችም።