በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች አማካሪ ዶ/ር ሚዛኔ አባተ የተመራ የኢሰመኮ የልዑካን ቡድን በኬንያ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (the Kenya National Commission on Human Rights) ከየካቲት 10 እስከ 13 ቀን 2018 ዓ.ም. በኬንያ፣ ናይሮቢ ስትራቴጂካዊ የልምድ ልውውጥና ጉብኝት አድርጓል፡፡ የልምድ ልውውጥና ጉብኝቱ የሁለቱ “ደረጃ-ሀ” (A-status) ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ትብብር ለማጠናከር እና የአቻ ለአቻ መማማርን ለማመቻቸት ያለመ ሲሆን ከየተቋማቱ የተውጣጡ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የቴክኒክ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የአራት ቀናት ቆይታ የነበረው ይህ መርኃ ግብር በተቋማቱ ዋና ዋና የሥራ ኃላፊነቶች እና አዳዲስ በሆኑና ቅድሚያ በሚሰጣቸው የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ ጠቃሚ መድረክ ሆኖ አገልግሏል። ውይይቱ የምክረ ሐሳቦች አፈጻጸምን ለመከታተልና ተግባራዊነታቸውን ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ሥርዓቶች፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለማረም ወይም ካሳ ለማስገኘት በሚቻልባቸው መንገዶች እንዲሁም በሽግግር ፍትሕ ሂደት የብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት በሚኖራቸው ሚና ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ በተጨማሪም የልዑካን ቡድኑ በምርጫ ዐውድ ውስጥ ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረጉ ተሳትፎዎችን፣ ሁሉ አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ወቅታዊ ግምገማ (Universal Periodic Review) ላይ የሚኖር ተሳትፎን እንዲሁም የተቋማዊ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ አዘገጃጀት እና የትግበራ ዝግጁነትን የተመለከተ ውይይት ተደርጓል።

በጉብኝቱ ኢሰመኮ ባለፉት 6 ዓመታት ነጻነቱን፣ ተደራሽነቱን እና ውጤታማነቱን ለማጠናከር ያከናወናቸውን አጠቃላይ የለውጥ ሥራዎች አብራርቷል። የልዑካን ቡድኑ በዲጂታል እና ነጻ የመረጃ ምንጮች (open source) ላይ የሚደረግ ምርመራን ለማሻሻል ያደረጋቸውን ጥረቶች፣ ተጨማሪ የከተማ ጽሕፈት ቤቶችን በማስፋፋት፣ የተደራሽነት ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ደግሞ ተጠሪዎችን (focal persons) በመመደብ፣ እንዲሁም ተንቀሳቃሽ የአቤቱታ ቅበላ ሥርዓትን በመዘርጋት የተቋሙን ተደራሽነት ከማስፋፋት አንጻር ያከናወናቸውን ተግባራት በዝርዝር አቅርቧል፡፡ ኢሰመኮ ከፌዴራል እና ከክልል መንግሥታት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የሚያካሂደው ቀጣይነት ያለው ከፍተኛ የውትወታ ሥራ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተቋማትና አጋሮች ጋር ያለው ግንኙነት ለኢሰመኮ ተቋማዊ ዐቅም መጠናከር አስተዋጽዖ ማድረጉ እና መንግሥት በተለያዩ ቁልፍ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ አዎንታዊ እርምጃ እንዲወስድ ማስቻሉ ተመላክቷል፡፡ ለአብነትም ኢሰመኮ እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት (United Nations office of the High Commisioner for Human Rights (UNOHCHR)) በትግራዩ ግጭት ያደረጉት የጋር የምርመራ ሪፖርት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ እንዲጸድቅ ከፍተኛ አስተዋጽዖ የነበረው መሆኑን የልዑካን ቡድኑ ጠቅሷል፡፡

የልዑካን ቡድኑ የኬንያ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሰብአዊ መብቶችን በማስፋፋት እና በመጠበቅ ረገድ በኬንያ ላሳየው የመሪነት ተግባር አድናቆቱን ገልጾ፣ ፍርድ ቤቶች ከገለልተኛ አካላት ሙያዊ አስተያየቶችን የሚቀበሉበትን ዘዴ (amicus curiae)፣ የሕግ ድጋፍ አገልግሎትን፣ በሕዝባዊ መብቶችና ጥቅሞች ላይ የሚደረጉ ክርክሮችን (public interest litigation)፣ ንግድ እና ሰብአዊ መብቶችን፣ የማረሚያ ቤቶችን መጨናነቅ ለመቀነስ ከእስራት ውጪ ያሉ ሌሎች አማራጭ ቅጣቶችን ተግባራዊነት እንዲሁም በዲጂታል ሥርዓት የታገዘና ተዓማኒነት ያለው የምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብቶች ክትትልን በተመለከተ ኢሰመኮ ከኬንያ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ልምድ ለመቅሰም ፍላጎቱን ገልጿል፡፡ የኢሰመኮ ልዑካን ቡድን ከኬንያ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር ካደረገው የልምድ ልውውጥ በተጨማሪ የኬንያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ጽሕፈት ቤት እና የምርጫ ታዛቢ ቡድንን የጎበኘ ሲሆን ተቋማቱም በኬንያ የምርጫ ማዕቀፍ ውስጥ ስላላቸው የሥራ ድርሻና ኃላፊነት ገለጻ ተድርጎለታል፡፡

ዶ/ር ሚዛኔ አባተ፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች አማካሪ

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የኬንያ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ ቀጣይነት ያለው ትብብር እና ግንኙነትን ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡