የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ታዳጊዎችን ማዕከል ያደረጉ ፖሊሲዎችን እና ፕሮግራሞችን መቅረፅ “ከማስረጃ ወደ ተጽዕኖ” ሲምፖዚየም ላይ ከሰኔ 2 እስከ 4 ቀን 2018 ዓ.ም. በኬኒያ ናይሮቢ ተሳትፏል። ሲምፖዚየሙ በምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የሚገኙ ታዳጊዎችን በተለይም ሴት ልጆችን ደኅንነት እና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሻሻል በማስረጃ፣ በፖሊሲ እና በፕሮግራም አተገባበር መካከል ያለውን ክፍተት ማጥበብ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ያለመ ነው። ፖሊሲ አውጭዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ተቋማት፣ የወጣቶች ማኅበራት እና የልማት አጋሮች በሲምፖዚየሙ ተሳትፈዋል።

በሲምፖዚየሙ Gender and Adolescence Global Evidence (GAGE) በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ግጭቶች እና አለመመጣጠኖች በታዳጊዎች ጤና እና ደኅንነት ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ የገመገመበት፤ የታዳጊዎችን ተሞክሮ ለመረዳትና ውጤታማ አተገባበርን ለመንደፍ የረጅም ጊዜ መረጃዎች ያላቸውን ጠቀሜታ፣ የታዳጊዎችን፣ ያለእድሜ ጋብቻን፣ የሴት ልጅ ግርዛትን እና የወጣቶችን ማኅበራዊና የፖለቲካ ተሳትፎ የተመለከቱ ጉዳዮችን የዳሰሰበትን ጥናት አቅርቦ ውይይት ተደርጓል።

በዚሁ መሠረት ኢሰመኮ በግጭት እና ድኅረ ግጭት ዐውድ በወጣቶች ላይ የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት የብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት ያላቸውን ሚና የተመለከተ የፓናል ውይይት ላይ ተሳትፏል። ውይይቱም በማስረጃ ላይ የተመሠረቱ፣ ተደራሽ እና የወጣቶች ነባራዊ ሁኔታ ላይ የተመሠረቱ ፖሊሲዎች እና ፕሮግራሞች አስፈላጊነት አጽንዖት ተሰጥቶታል። ኢሰመኮ ግጭት ባለባቸው በተለይም በአማራ እና ትግራይ ክልሎች ካከናወናቸው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል እና ምርመራ ሥራዎች የለያቸውን ግኝቶች ያካፈለ ሲሆን፤ በግጭት እና ድኅረ ግጭት ዐውድ ማገገሚያ ወቅት ታዳጊዎችን ለመጠበቅ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችንም አጉልቶ አሳይቷል። ኢሰመኮ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና የሰብአዊ መብቶች ጥበቃን ለማጠናከር ሕዝባዊ መድረኮችን በማካሄድ ረገድ ያለውን ተሞክሮ አካፍሏል። በተጨማሪም በGAGE የቀረበው የጥናት ውጤት የሲት ልጅ ግርዛትን ለመግታት በሚያከናውናቸው ተግባራት እና ስር የሰደዱ ተግዳሮቶችን በመለየት የፖሊሲ ማሻሻያ ውትወታዎችን ለማጠናከር ጠቃሚ ግብዓት እንደሆነ አመላክቷል።

ሲምፖዚየሙ ኢሰመኮ ከተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ከወጣቶች ተወካዮች ጋር የልምድድ ልውውጥ ማድረግ ያስቻለ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። ከማስረጃ ማመንጨት በማስረጃ ላይ ወደተመሠረተ ተግባር መሸጋገር ያለው አስፈላጊነት ከሲምፖዚየሙ የተገኘ ቁልፍ ትምህርት ሲሆን፤ የጥናት ግኝቶችን በውትወታ፣ በክትትል፣ በምርመራ፣ በሕዝባዊ መድረኮች እና በውሳኔ ሐሳቦች ውስጥ ማካተት በታዳጊዎች ሕይወት ላይ ተጨባጭ መሻሻሎችን ለማረጋገጥ ያለው ጠቀሜታም የታየበት ነው።