የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መጋቢት 1 ቀን 2018 ዓ.ም. በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጋሞ ዞን፣ ጋጮ ባባ፣ ቦንኬ፣ ካምባ ዙሪያ እና ምዕራብ አባያ ወረዳዎች በሚገኙ 6 የተለያዩ ቀበሌዎች የተከሰቱ የመሬት መንሸራተት፣ የናዳ እና የጎርፍ አደጋዎችን ተከትሎ የደረሱ ጉዳቶችን እየተከታተለ ይገኛል። በዚህም በሰዎች ሕይወት፣ አካል ደኅንነት እና ንብረቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ለማረጋገጥ የቻለ ሲሆን፣ ይህ መግለጫ ይፋ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ በድምሩ የ65 ሰዎች ሕይወት ማለፉ እና አስከሬናቸው መገኘቱ የተረጋገጠ ሲሆን ቀሪ 60 ሰዎች ደግሞ የገቡበት ባለመታወቁ በአደጋው ሕይወታቸው ማለፉ እንደሚገመት ለመረዳት ችሏል። በተጨማሪም 3461 ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው ለከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ መጋለጣቸውን እንዲሁም ሙሉ በሙሉ የወደሙ መኖሪያ ቤቶች እና ማሳዎችን ጨምሮ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ኢሰመኮ አረጋግጧል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና የጋሞ ዞን የአደጋ ሥጋት አመራር ግብረ ኃይል የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በመለየት፣ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስፈልጉ አቅርቦቶችን በአስቸኳይ ለማሟላት ኮሚቴዎች አዋቅሮ ወደ ሥራ መግባቱን ለማወቅ ተችሏል። ኢሰመኮ ይህንን ጨምሮ በክልሉና በዞኑ አስተዳደር እየተወሰዱ የሚገኙ መልካም እርምጃዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እያሳሰበ፤ ተፈናቃዮች አስቸኳይ ምግብ፣ ውሃ፣ ሕክምና እና ጊዜያዊ መጠለያን ጨምሮ አስፈላጊ አቅርቦቶችን ያለምንም መዘግየት እንዲያገኙ ለማድረግ እና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥት ተቋማት እንዲሁም ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች አፋጣኝ እና የተቀናጀ ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀርባል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በደረሰው ጉዳት የተሰማቸውን ከፍተኛ ሐዘን ገልጸው፣ ለአደጋው የሚሰጠው ምላሽ ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ፣ የተቀናጀ እና በአፋጣኝ የሚከናወን እንዲሁም እንደ ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ያሉ ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ፍላጎት ያማከለ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል። ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም በቀጣይ መሰል ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሊያስከትሉት የሚችሉትን አደጋ ለመቀነስ እና ከመከሰታቸው አስቀድሞ ለመከላከል በልዩ ትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ ኢሰመኮ ክትትሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ግኝቶችን መሠረት በማድረግ ዝርዝር የመፍትሔ ሐሳቦችን ለሚመለከታቸው አካላት እንደሚያቀርብ አረጋግጠዋል።