የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መገናኛ ብዙኃን ቁጥጥር ሥርዓት የሴቶች እና የሕፃናት መብቶችን ከማስጠበቅ አንጻር ያሏቸው መልካም ተሞክሮዎች እና ክፍተቶች ላይ ያተኮረ ምክክር የካቲት 13 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል። ምክክሩ በርዕሰ ጉዳዩ ዙሪያ ባለድርሻ አካላት ያላቸውን ግንዛቤ ለማጎልበት ያለመ ነው፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት፣ ብሮድካስት መገናኛ ብዙኃን፣ የሕፃናት ፓርላማ እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች በምክክሩ ተሳትፈዋል።

በመድረኩ የመገናኛ ብዙኃን ቁጥጥር ምንነት፣ በመገናኛ ብዙኃን የሚሰራጩ ይዘቶች እና የቁጥጥር ሥርዓት የሴቶችን እና የሕፃናትን መብቶች ከማስጠበቅ አኳያ የታዩ አበረታች ሁኔታዎች እና መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ለውይይት መነሻ የሚሆን ዝርዝር ማብራሪያ ቀርቧል።
በቀረበው መነሻ ሐሳብም መገናኛ ብዙኃንን የተመለከቱ ፖሊሲዎችና ሕጎች የሴቶች እና የሕፃናት ጉዳዮችን በሚገባው ጥልቀት አለማካተታቸው፤ በቂና ተከታታይነት ያለው የዐቅም ግንባታ ስልጠና አለመኖር፤ በብሮድካስት አገልግሎት ተቋማት ላይ ቁጥጥር የማድረግ ሥልጣንና ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት የሚያከናወኑት ግምገማና ክትትሎች በቂ አለመሆናቸው፣ ውይይቱ በተካሄደበት ወቅት ከአንድ የመገናኛ ብዙኃን ተቋም ውጪ ሌሎቹ የሥርዓተ ጾታ ፖሊሲ የሌላቸው መሆኑ፣ የሴቶች እና የሕፃናት ጉዳዮችን ቅድሚያ በመስጠት በቂ የአየር ሽፋን መመደብ ላይ ክፍተት መኖሩ፣ በሴት ጋዜጠኞች ላይ የሚደርስ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት በክፍተትነት የቀረቡ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ሕፃናትን የተመለከቱ ይዘቶች የሕፃናትን ጥቅም፣ ክብር፣ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እና ፈቃደኝነት ከማረጋገጥ አንፃር ክፍተቶች ያሉባቸው መሆኑ ተነስቷል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች ተቆጣጣሪ አካላት መገናኛ ብዙኃን የሴቶች እና የሕፃናት መብቶችን ያከበሩ እንዲሆኑ መደበኛና ስልታዊ ክትትል እና ቁጥጥር ማከናወን፣ ራሱን የቻለ የመገናኛ ብዙኃን ሥርዓተ ጾታ ፖሊሲ መቅረጽና ተግባራዊ ማድረግ፣ ሴቶች በመገናኛ ብዙኃን አመራርነት፣ ባለሙያነት እንዲሁም የኤዲቶሪያል ቡድን አባልነት ያላቸውን ውክልናና ተሳትፎ ማሳደግ፣ የግንዛቤ ማሳደግ ሥራዎችን በትብብር መሥራት፣ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ሪፖርት የሚደረግበት ሥርዓት መዘርጋት እና ሕፃናትን በተመለከተ የሚሠሩ ዘገባዎችን አካታችነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተከበሩ አቡኔ አለም በመገናኛ ብዙኃን መካከል ትስስር በመፍጠር በሕግና አፈጻጸም ረገድ የተጠቀሱ ችግሮችን ለመፍታት ተገቢውን ጥናት በማድረግ ለሚመለከተው አካል ማድረስ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ አክለውም ቋሚ ኮሚቴው ከምክክር መድረኩ ለቀጣይ ሥራዎች ግብአት የሚሆኑ ሐሳቦች እንደወሰደና ስምምነት ላይ የተደረሰባቸውን ነጥቦች ተግባራዊ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስፈላጊውን የክትትልና ቁጥጥር ሥራ እንደሚያከናውን ጠቁመዋል፡፡

የኢሰመኮ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ በውይይት የተነሱ የሕግና የአፈጻጸም ክፍተቶችን መሠረት በማድረግ ቀጣይ ሥራዎችን ለማሳካት የመገናኛ ብዙኃን፣ የመገናኛ ብዙኃን ተቆጣጣሪ አካላት እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ እና በቅንጅት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል። አክለውም ኢሰመኮ በጉዳዩ ላይ የክትትልና ምክክር ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጸዋል።